ቀጥታ፡

በተጠባቂው ጨዋታ ኮትዲቯር እና ካሜሮን ነጥብ ተጋሩ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ስድስት ጨዋታ ኮትዲቯር እና ካሜሮን አቻ ተለያይተዋል።

ማምሻውን በማራካሽ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የማንችስተር ዩናይትዱ አማድ ዲያሎ በ51ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ግብ ኮትዲቯርን መሪ አድርጓል። አማድ በውድድሩ ላይ ሁለተኛ ግቡን ማስቆጠር ችሏል።

የኮትዲቯሩ ተከላካይ ጊስላን ኮናን በ56ኛው ደቂቃ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ግብ ካሜሮን አቻ ሆናለች።

በ48ኛው ደቂቃ የኮትዲቯሩ ፍራንክ ኬሲ ያስቆጠራት ግብ በቪዲዮ በታገዘ ዳኝነት (ቫር) ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ተሽሯል።

ጨዋታው እንደ ተጠባቂነቱ ጠንካራ ፉክክር ተደርጎበታል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ(ዶ/ር) በስታዲየሙ ተገኝተው ጨዋታውን ተመልክተዋል።

የሪያል ማድሪድ ተጫዋቾች የሆኑት ኪሊያን ምባፔ እና ኦሪየር ቹዌሜኒ (ሁለቱም በትውልድ ካሜሮናዊ በዜግነት ፈረንሳዊ)፣ የካሜሮን የቀድሞ ተጫዋች አሌክሳንደር ሶንግ እንዲሁም የባርሴሎናው ጁል ኩንዴ (በትውልድ ቤኒናዊ በዜግነት ፈረንሳዊ) ጨዋታውን በስታዲየም ተገኝተው ተከታትለዋል።

የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የቀድሞ ተጫዋች ሳሙኤል ኤቶ በስታዲየሙ ታድሟል።

ጨዋታውን ከ35 ሺህ በላይ ተመልካቾች ተከታትለውታል።

ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ኮትዲቯር እና የአምስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ካሜሮን በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ኮትዲቯር እና ካሜሮን አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ዛሬ በምድብ ስድስት በተደረገ ጨዋታ ሞዛምቢክ ጋቦንን 3 ለ 2 አሸንፋለች።

የምድብ ስድስት የመጨረሻ መርሃ ግብር ረቡዕ ታህሳስ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። ጋቦን ከኮትዲቯር እና ሞዛምቢክ ከካሜሮን ይጫወታሉ።

ጨዋታዎቹ በምድቡ ወደ ጥሎ ማለፍ የሚገቡ ሀገራትን የሚለዩ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም