የምስራቅ አፍሪካዋ ሱዳን ኢኳቶሪያል ጊኒን በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሏን አስመዘገበች - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካዋ ሱዳን ኢኳቶሪያል ጊኒን በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሏን አስመዘገበች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አምስት ጨዋታ ሱዳን ኢኳቶሪያል ጊኒን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ማምሻውን በመሐመድ አምስተኛ በተካሄደው ጨዋታ የኢኳቶሪያል ጊኒው ተከላካይ ሳውል ኮኮ በ73ኛው ደቂቃ በራሱ መረብ ላይ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
ኢኳቶሪያል ጊኒ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ብትወስድም ሱዳን በፈጣን ሽግግር እና መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ እድሎችን ፈጥራለች።
ውጤቱን ተከትሎ ከአፍሪካ ዋንጫ መስራች ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሱዳን በዘንድሮው ውድድር የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባለች። በምድብ አምስት በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።
በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እየተሳተፉ ከሚገኙ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ሱዳን የመጀመሪያን ድል ያገኘች ሀገር ሆናለች።
ታንዛንያ እና ዩጋንዳ ሌሎች ተሳታፊ ሀገራት ናቸው።
በምድቡ ሁለተኛ ሽንፈቷን ያስተናገደችው ኢኳቶሪያል ጊኒ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዛለች።
በምድብ አምስት አልጄሪያ ከቡርኪናፋሶ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 በፕሪንስ ሙላይ ኤል ሀሰን ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።