ለትውልድ ግንባታ ጉልህ ሚና ያላቸውን መሰረተ ልማቶች ማስፋፋት ቅድሚያ ተሰጥቶታል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ለትውልድ ግንባታ ጉልህ ሚና ያላቸውን መሰረተ ልማቶች ማስፋፋት ቅድሚያ ተሰጥቶታል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፦ ለትውልድ ግንባታ ጉልህ ሚና ያላቸውን መሰረተ ልማቶች ማስፋፋት ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች በአዲስ አበባ ከተማ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተገነባውን የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የህጻናት መጫወቻና የህዝብ መዝናኛ ቦታን ስራ አጀምረዋል።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አዲስ አበባን ተወዳዳሪ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ልማት ስራዎች ውጤት እያመጡ ነው።
ከልማቱ ጎን ለጎን የወጣቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ለትውልድ ግንባታ አስተዋጽኦ ላላቸው መሰረተ ልማቶች ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
ዛሬ የተመረቀው በ10 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የህጻናት መጫወቻና መዝናኛ ቦታ ለተሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ብቻ 23 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች መገንባታቸውን አስታውሰው፤ መሰል የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራዎች በሌሎች ክፍለ ከተሞች በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
በአግባቡ ስራ ላይ ያልዋሉ ቦታዎች ምቹ እና ጹዱ በማድረግ ህዝቡ እንዲጠቀም የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።