የቻይና ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው-አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው-አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፦ የቻይና ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ገለጹ።
የኢትዮጵያን ቡናን በቻይና ገበያ የበለጠ ለማስተዋወቅ እና ኤክስፖርቱን ለማሳደግ ያለመ ኮንፍረንስ በቻይና ሁናን ግዛት እየተካሄደ ነው።
ኮንፍረንሱ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ እና ቻይና ጠንካራ ግንኙነት የሚያሳይ ሲሆን ወዳጅነታቸው በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት(all-weather strategic partnership) ምዕራፍ መሸጋገሩም ተገልጿል።
ሁነቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካን ጥልቅ የኢኮኖሚ አቅም እንደሚያሳይ ተነግሯል።
ቻይና የኢትዮጵያ ቡና ዋና መዳረሻ እየሆነች የመጣች ሲሆን የዛሬ አምስት አመት የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ከነበረችበት 33ኛ ደረጃ በተያዘው አመት ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ብላለች።
የቻይና ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ በወቅቱ ገልጸዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው በበኩላቸው፥ እያደገ የመጣውን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት በማንሳት ቡናም አንድ አስተሳሳሪ እየሆነ መምጣቱን አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በግብርና መስክ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትን በማንሳት በግብዓት፣ በውጤታማ የምርት አሰባሰብ፣ ክምችትና ሥርጭት መስኮች ተባብሮ ለመስራት ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ቡና ለኢትዮጵያ ምርት ብቻ ሳይሆን ባህላዊ እሴትም መሆኑን በመግለፅ የሁለቱን ሃገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ አንስተዋል።
ኮንፍረንሱ ቻይና በኢትዮጵያ ቡና ያላትን ተደራሽነት የበለጠ ለማሳደግና ወደ ቻይና የሚላከውን የቡና ኤክስፖርት መጠን ማሳደግ ያለመ መሆኑን ኢዜአ ከስፍራው ያገኘው ያመለክታል።