ቀጥታ፡

የሙያ ክህሎትን በመጠቀም በአነስተኛ ካፒታል የተጀመረ የስኬት መንገድ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፦ የሙያ ክህሎትን በመጠቀም በአነስተኛ ካፒታል የተጀመረ የስኬት መንገድ የሥራ ቅጥር ከመፈለግ በርካታ ሰዎችን ወደ መቅጠር እንዳሸጋገራቸው በተለያየ የሙያ መስክ ሥራ ፈጣሪዎች ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ ያዘጋጀው የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ተጠናቋል።

''ድምቅ በኢትዮጵያ ምርት" በሚል መሪ ሃሳብ ከታህሣስ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በቆየው ባዛር ላይ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎቶች ቀርበዋል።

በኤግዚቢሽኑና ባዛሩ ላይ የተሳተፈው ኢምራን ሙህዲን፤በእንጨት የቅርፃ ቅርፅ ፈጠራ ሥራ ከእራሱ አልፎ ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል። 

በተሰማራበት አነስተኛ ሥራ የእንጨት ቅርፃ ቅርፅ የምርት ውጤቶችን በስፋት ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ እንደሚገኝ ተናግሯል። 

በተመሳሳይ በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ የሹራብ ምርት ውጤቶችን ያቀረቡት ሃና መዴ፤ በአነስተኛ የገንዘብ መጠን የጀመሩት ሥራ ለሌሎች የሥራ ዕድል ያመቻቹበትን ውጤታማ አቅም መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

የፈጠሩት የሙያ ሽግግርም  በአነስተኛ መነሻ ገንዘብ አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ጌጠኛ የክር ዘምቢል፣ ምንጣፍና ተያያዥ የፈጠራ ምርት ውጤቶችን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችን እያደገ ነው ያሉት ደግሞ በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የተሳተፉት ቃል-ኪዳን ታደመ ናቸው።

የማምረቻ ማሽኖችን ከውጭ በማስገባት አስራ አምስት እናቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የተሳተፉት ሌላኛዋ የፈጠራ ባለቤት ኤደን ኃይሉ፤ በአንድ ማሽንና በአነስተኛ ካፒታል በጀመርኩት የቆዳ ውጤቶች የማምረት ሥራ አሁን ላይ ከፍተኛ ዕድገት አስገኝቶልኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከራሳቸው አልፎ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ማመቻቸታቸውን አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም