ቀጥታ፡

በሀዋሳ ከተማ የሚከበሩ ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ለከተማዋ ቱሪዝም ዕድገት ትልቅ አበርክቶ አላቸው- ከንቲባ ጥራቱ በየነ

ሀዋሳ ፤ታህሳስ 19/2018 (ኢዜአ) ፡-የሀዋሳ ከተማ ካላት የተፈጥሮ መስህብ በተጨማሪ በከተማዋ የሚከበሩ ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ለከተማዋ ቱሪዝም ዕድገት ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ።

ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል በሀዋሳ ተከብሯል።


 

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማው ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እንዳሉት የሀዋሳ ከተማ ካላት የተፈጥሮ መስህብ በተጨማሪ በከተማዋ የሚከበሩ ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ለከተማዋ ቱሪዝም ዕድገት ትልቅ አበርክቶ አላቸው።

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል በከተማችን በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ እንግዶች የሚሳተፉበት በመሆኑ ከተማዋ በጉጉት የምትጠብቀው ነው ብለዋል።

በዓሉ ለከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ያለው አበርክቶ ከፍ ያለ ነው ያሉት አቶ ጥራቱ በከተማዋ የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሃይማኖታዊ መስህብ ስፍራዎች የቱሪዝም ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የጎላ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል።

ሀዋሳ የመንፈሳዊ ክብረ በዓላት፣ የስብሰባና ሌሎች ሁነቶች የሚካሄዱባት የቱሪስት ከተማ መሆኗን ጠቅሰው የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍና አህጉራዊ ኮንፈረንስ የሚካሄድባት ከተማ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሀገራችን በተፈጥሮ ከታደሉ ከተሞች አንዷ የሆነችው ሀዋሳን የበለጠ ውብ፣ ሳቢና ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።


 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሰላማ በበኩላቸው ምዕመኑ ለሀገራችን ሰላም በህብረት በመፀለይ መትጋት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በበዓሉ ላይ ከታደሙት ውስጥ ከአዳማ እንደመጣች የተናገረችው ወጣት ቃልኪዳን እምባዕ በሀዋሳ ባየሁት የህዝብ አቀባበል በጣም ደስተኛ ነኝ ብላለች።


 

በቀጣይ በዓሉን ለመታደም በየዓመቱ ለመምጣት ዕቅድ እንዳላት የተናገረችው ወጣት ቃልኪዳን የሀዋሳ ህዝብ ላደረገላት አቀባበልና መስተንግዶም ምስጋናዋን አቅርባለች።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም