ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ተፋሰሶችን በማልማት የሥራ እድል መፍጠሪያ የማድረግ ጥረት ይጠናከራል

ከሚሴ ፤ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ተፋሰሶችን በማልማት የሥራ እድል መፍጠሪያ የማድረግ ጥረት እንደሚጠናከር በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ገለፁ።

በክልሉ የ2018 ዓ.ም የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ በከሚሴ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ እንደገለፁት፣ በክልሉ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እየተገኘ ያለውን ውጤት አጠናክሮ በመቀጠል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል።

በቀጣይም ተፋሰሶችን በማልማት የሥራ እድል መፍጠሪያ የማድረግ ጥረት የበለጠ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

ለዚህም ቀደም ሲል የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም ህብረተሰቡን ማሳተፍና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ልማቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ውጤት እያመጣ በመሆኑ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንሰሳት መኖና በሌሎችም የተሻለ ለመስራት መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ በበኩላቸው፣ ተፋሰሶችን በማልማት የገቢ ምንጭ ጭምር እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የተፋሰስ ልማት የተከናወነባቸው አካባቢዎችን ከእንሰሳት እና ከሰው ንክኪ ነጻ በማድረግም በፍራፍሬ እየለሙ መሆኑን ገልጸዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን እንዳሉት፣ በዞኑ በ1 ሺህ 52 ተፋሰሶችን ያካተተ 71 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ ተገብቷል።

ህብረተሰቡ ተፋሰሶችን እንዲጠብቅና ዘላቂ በማድረግ ቋሚ የገቢ ምንጭ መሆን እንዲችሉም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የህልውና ጉዳይ አድርጎ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀሰን ሰይድ ናቸው።

ባለፉት አመታት በተሰሩ ሥራዎች የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ዘንድሮ በ286 ተፋሰሶች መሰረት ያደረገ 15 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራሮች ፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም