መንግሥት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚያከናውናቸው ተግባራት የበኩላችንን ሚና እየተወጣን ነው-አምራቾች - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚያከናውናቸው ተግባራት የበኩላችንን ሚና እየተወጣን ነው-አምራቾች
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 19/2018 (ኢዜአ)፦መንግስት የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚያከናውናቸው ተግባራት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን አምራቾች ገለፁ።
ሁለተኛው የብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ (ግሪን ሞቢሊቲ) ዐውደ ርዕይና ፎረም 2025 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተከፍቷል።
በዐውደ ርዕዩ ምርታቸውን እያስተዋወቁ ከሚገኙት መካከል የቤካ ግሩፕ ማኔጂነግ ዳይሬክተር ሚካኤል ካሳ እንደገለጸው፤ በኤግዚቢሽኑ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልልቅ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለመገጣጠም በሥራ ላይ የሚገኝ ፕሮጀክት ይዘው ቀርቧል።
በአሁኑ ወቅትም ሻክማን ከሚባል የቻይና ኩባንያ የመገጣጠም ስራውን መጀመሩን ገልጸው፤ ከአራት ወር በኋላም ወደ ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው፤ አውደ ርዕዩ ኩባንያው የሚገጣጥማቸውን በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማስተዋወቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በኤክስፖው ላይ ወጭ ቆጣቢና የአየር ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መቅረባቸውን ገልጸው፤ በዚህም የራሱን ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከስታንዳርድ እስከ ፖሊሲ በማውጣት በታዳሽ ሀይል ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ልዩ ትኩረት መስጠቷን ገልጸው፤ ይህም በአፍሪካ የመሪነት ሚና እንድትወጣ አስችሏታል ብለዋል።
በ2030 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር 500 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ አውደ ርዕዩ ለዚህ የሚያስፈልጉ ኢንቨስትመንቶች እና ትብብሮችን ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።