በዞኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሰብል አሰባሰብ ወቅት የሚደርሰውን የምርት ብክነት ለመቀነስ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሰብል አሰባሰብ ወቅት የሚደርሰውን የምርት ብክነት ለመቀነስ ትኩረት ተደርጓል
ሮቤ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ) :-በባሌ ዞን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሰብል አሰባሰብ ወቅት የሚደርሰውን የምርት ብክነት ለመቀነስ ትኩረት መደረጉን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ እንዳሉት በዞኑ በመኸሩ ወቅት በተለያዩ ሰብሎች የለማውን 538 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ምርት የመሰብሰቡ ሂደት እየተከናወነ ነው።
በቴክኖሎጂ የታገዘው የሰብል ስብሰባው ሂደት በድህረ ምርት ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት ብክነት ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም የደረሰውን ሰብል ለመሰብሰብ በዞን ደረጃ ከ380 የሚበልጡ ኮምባይነሮች መሰማራታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
የመኸር አዝመራውን በመካናይዜሽን በመታገዝ ምርቱን የመሰብሰብ ስራው በዋናነት በዞኑ ሲናና እና ጋሠራ ወረዳዎች በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ እስከ አሁን በተደረገው ጥረት በመኸሩ ወቅት በዋና ዋና ሰብሎች ከለማው አጠቃላይ መሬት መካከል 65 ሺህ ሄክታር ላይ የለማው ሰብል ተሰብስቧል።
ከተሰበሰበው ሰብል ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የጠቀሱት ምክትል ኃላፊው፤ ከአጠቃላይ ልማቱ ከ19 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አክለዋል።
የደረሰን ሰብል ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመታደግ በኮምባይነር እየተደረገ ካለው የሰብል ስብሰባ በተጓዳኝ በአነስተኛ ማሽነሪዎችና በሰው ጉልበት የመሰብሰቡ ሥራም ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው የተናገሩት።