ቀጥታ፡

የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓልን በአብሮነትና ሐይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ አክብረነዋል-የእምነቱ ተከታዮች

ቁልቢ፤ታህሳስ 19/2018 (ኢዜአ)፦ዓመታዊ የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓልን በአብሮነት፣ በመደጋገፍና ሐይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ማክበራቸውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታዮች ገለፁ።

የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ያከናወኑት ተግባር በዓሉ በስኬት እንዲከበር የራሱን ድርሻ ማበርከቱም ተመልክቷል።

በበዓሉ ላይ ያገኘናቸው የእምነቱ ተከታዮች እንደገለፁት፤ የዘንድሮውን የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል በአብሮነት፣በመደጋገፍና ሐይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ አክብረዋል።

ቁልቢ ገብርኤል በየዓመቱ እንደሚያከብር የገለፀው ሳሙኤል ብርሃነ፥ በዓሉን በመቻቻልና ኢትዮጵያዊ አብሮነትን በሚያሳይ መልኩ ማክበሩን ተናግሯል።

የአካባቢው ማህበረሰብ እና የፀጥታ አካላት ለምዕመናኑ ላደረጉት አቀባበል፣ድጋፍና ትብብር ምስጋና ያቀረቡት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በንግስ ባዓሉ ላይ የተገኙት ወይዘሮ አየለች በየነ ናቸው።

በማህበረሰቡ የተደረገላቸው አቀባበል እንዳስደመማቸው ገልፀው፥ በዓሉንም በአብሮነትና በመደጋገፍ ማክበራቸውን አክለዋል።

ወጣት ሃይለሚካኤል ስዩም በበኩሉ፥ ከዋዜማው ጀምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተገኘን ምዕመናን በዓሉን ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ፣ በደስታና እርስ በርስ በመደጋገፍ አክብረነዋል ብሏል።

ከ1984 ጀምሮ በየዓመቱ ወደ ገዳሙ እንደሚመጡ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ግዛው፥ በዓሉን ኃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ማክበራቸውን ገልፀዋል።

ትልቅ መተሳሰብ እና መደጋገፍ የታየበት በዓል እንደነበርም ምዕመኑ ተናግረዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊና እና የበዓሉ አከባበር ፀጥታ ግብረ ሃይል አስተባባሪ ረዳት ኮሚሽነር ናስር መሀመድ እንደተናገሩት፤ በዓሉ ያለምንም ችግር በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

እስካሁንም አንድም የትራፊክ አደጋ እና የወንጀል ድርጊት እንዳልተከሰተ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ የአካባቢው ማህበረሰብም ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ያከናወኑት ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ያከናወኑት ተግባር በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ማስቻሉንም ረዳት ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም