ቀጥታ፡

አፍሪካውያን ሀገር በቀል አሰልጣኞች ጎልተው የታዩበት የአፍሪካ ዋንጫ !

35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።24 ሀገራት በስድስት ምድቦች ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው።

በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ 24 ሀገራት 12ቱ በአፍሪካውያን የሚሰለጥኑ ናቸው።

የአዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ ከዛው ከሀገራቸው ናቸው። የ50 ዓመቱ አሰልጣኝ በ22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሞሮኮን ለግማሽ ፍጻሜ አድርሰዋል።ሀገሪቷ በዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሀገር ሆናለች።

ከእ.አ.አ 2022 አንስቶ ብሄራዊ ቡድኑን እየመሩት የሚገኙት ሬግራጉዊ ሞሮኮን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኮትዲቭዋር አሰልጣኝ የ41 ዓመቱ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋች ኤመርሰን ፋኤ ነው።

ፋኤ እ.አ.አ በ2023 በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት በተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን በመምራት ዋንጫውን እንዲያነሳ አድርጓል።

በውድድሩ መሐል በውጤት ማጣት የተሰናበቱትን ፈረንሳዊውን አሰልጣኝ ጂን-ሉዊስ ጋሴት በመተካት በጊዜያዊነት አሰልጣኝ የተሾመው ፋኤ ቡድኑን ለዋንጫ ማብቃቱ አስወድሶታል።

በዘንድሮው ውድድር ዋንጫውን ለማንሳት የቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት ተርታ የተመደበችው ሴኔጋል አሰልጣኝ የ41 ዓመቱ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ፓፔ ታው ነው።

ፓፔ ታው በተጫዋችነት ዘመኑ ለሴኔጋል ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች አምስት ግቦችን አስቆጥሯል።

አሰልጣኙ ሴኔጋል ለ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ እንድታልፍ አድርጓል። ከሶስት ዓመት በፊት በአልጄሪያ በተካሄደው የሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) ሴኔጋል ዋንጫውን ስታነሳ የቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ መርቷል።

የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ግብጽ የምትሰለጥነው በቀድሞ ኮከቧ ሆሳም ሀሰን ነው። በተጫዋችነት ዘመኑ በአፍሪካ ዋንጫ 11 ግቦችን አስቆጥሯል። በ177 ጨዋታዎች 69 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የብሄራዊ ቡድኑ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።

ሆሳም ሀሰን የአፍሪካ ዋንጫን ሶስት ጊዜ በተጫዋችነት በማንሳት ስኬታማ አሰልጣኝ ነው።

ሌላኛው የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ካሜሮን አሰልጣኝ የ56 ዓመቱ ዴቪድ ፓጉ ነው። ካሜሮናዊው አሰልጣኝ የተሾሙት ከሰሞኑ ነው። ቤልጂየማዊውን አሰልጣኝ ማርክ ብራይስን በመተካት ቡድኑን እንዲመሩ ኃላፊነት ተጠሎባቸዋል።

በካሜሮን እግር ኳስ ባላቸው የታክቲክ መረዳት እና ብቃት የሚሞካሹት ፓጉ ቡድኑን አንድ በማድረግ የተሻለ ውጤት ያመጣሉ የሚል እምነት ተጥሎባቸዋል።

ሌላኛው የውድድሩ ተሳታፊ ሀገር ዛምቢያ ናት።የ48 ዓመቱ የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን የቀድሞ ተከላካይ ሞሰስ ሲቾኔ የቡድኑ የወቅቱ ዋና አሰልጣኝ ናቸው።

ከእ.አ.አ 2022 እስከ 2024 በጊዜያዊነት እና በረዳት አሰልጣኝነት ያገለገሉት ሲቾኔ በ2025 ዋና አሰልጣኝ ሆነው ተሾመዋል።

ምስራቅ አፍሪካን በውድድሩ ከሚወክሉ ሶስት ሀገራት መካከል አንዷ ሱዳና ናት። ጋናዊው ጀምስ ክዌሲ አፒያ የቡድኑ አሰልጣኝ ናቸው። አፒያ ከእ.አ.አ 2023 አንስቶ ቡድኑን እያሰለጠኑ ይገኛሉ።

የጋቦን አሰልጣኝ ቲዬሪ ሞዩማ የብሄራዊ ቡድኑ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ነበር። ለ11 ዓመታት ለጋቦን ተጫውተዋል። ከእ.አ.አ 2023 አንስቶ ብሄራዊ ቡድኑን በአሰልጣኝነት እየመሩ ይገኛል።

የ44 ዓመቱ ደቡብ አፍሪካዊ ሞሬና ራሞሬቦሊ የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ናቸው። ከእ.አ.አ 2025 አንስቶ ቡድኑን እያሰለጠኑ ይገኛል። ሞሬና ከዚህ ቀደም የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነበሩ።

የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቡርኪናፋሶ አሰልጣኝ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን የአማካይ ተጫዋች ብራማ ትራኦሬ ነው። አሰልጣኙ ከእ.አ.አ ማርች 2024 አንስቶ ቡርኪናፋሶን እየመራ ይገኛል። ትራኦሬ ቡድኑ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

የአንድ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የሆነችው ቱኒዚያ አሰልጣኝ የቀድሞ የቡድኑ የተከላከይ መስመር ተጫዋች ሳሚ ትራቤልሲ ናቸው። የ57 ዓመቱ አሰልጣኝ ለቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን ለ10 ዓመታት በተጫዋችነት አገልግሏል። ብሄራዊ ቡድኑን ከእ.አ.አ 2025 ቱኒዚያን እየመራ ይገኛል።

በአፍሪካ ደቡባዊ ክፍል የምትገኘው ሞዛምቢክ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

ፍራንቺስኮ ኩዌሪዮል ኮንዴ ጁኒየር (ቺኩዊኒዮ ኩንዴ) የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ናቸው። የ60 ዓመቱ አንጋፋ አሰልጣኝ ለሞዛምቢክ ለ15 ዓመታት በተጫዋችነት አገልግለዋል። ለሀገራቸው በ43 ጨዋታዎች 12 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ኩንዴ ከእ.አ.አ 2021 አንስቶ ብሄራዊ ቡድኑን እያሰለጠኑ ይገኛሉ።

የናይጄሪያ አሰልጣኝ የሆነው ኤሪክ ቼሌ የኮትዲቭዋር፣ ማሊ እና ፈረንሳይ ጥምር ዜግነት ያላቸው አሰልጣኝ ናቸው። ይሁንና ቼሌ የአፍሪካ የዘር ግንድ ቢኖራቸውም በፈረንሳይ መወለዳቸው የውጭ ሀገር ዜጋ ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።

የአፍሪካውያን አሰልጣኞች በአፍሪካ ዋንጫ የማሰልጠን ምጣኔ ከሌሎቹ ወቅቶች አንጻር የአሁኑ የተሻለ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ሀገር በቀል አሰልጣኞች እየተሰጣቸው ያለውን ትኩረት ያሳያል።

12 ሀገራት በውጭ ሀገር ዜጎች ይሰለጥናሉ።

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ አፍሪካውያን የሚያሰለጥኗቸው ወይስ የውጭ ሀገር ዜጋዎች የሚመሯቸው ሀገራት ዋንጫውን ያነሳሉ? የሚለው ጉዳይ ትኩረትን ስቧል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም