የትህነግ ቡድን የመልሶ ማቋቋም ሥራን በማደናቀፍ ተፈናቃዮችን የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረገ ነው-የስምረት ለዲሞክራሲ ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
የትህነግ ቡድን የመልሶ ማቋቋም ሥራን በማደናቀፍ ተፈናቃዮችን የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረገ ነው-የስምረት ለዲሞክራሲ ፓርቲ
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 19/2018 (ኢዜአ)፡-የትህነግ ቡድን የመልሶ ማቋቋም ሥራን በማደናቀፍ ተፈናቃዮችን የሴራ ፖለቲካው መጠቀሚያ እያደረገ መሆኑን የስምረት ለዲሞክራሲ ፓርቲ ገለጸ።
ሕገ ወጥ ቡድኑ የእርዳታ እህል ለተፈናቃዮች እንዳይደርስ በማድረግ ረሃብ ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን አመልክቷል።
የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምክር ቤት እና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አባል ጣዓመ ዓረዶም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፥ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ሕገወጥ ቡድን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዳይቋቋሙ እንቅፋት ፈጥሯል።
ተፈናቃዮችንም የሴራ ፖለቲካው መጠቀሚያ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕገወጥ ቡድኑ ለፖለቲካ ትርፍ ሲል በተፈናቃዮች ስም እንደሚነግድ አመልክተው፤ ተፈናቃዮችን በማስፈራራትና ችግር ውስጥ በማስገባት ለርሃብ እየዳረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ሕገ ወጥ ቡድኑ ለተፈናቃዮች የሚላከውን እርዳታ በመቀማት ለፖለቲካ ዓላማ እያዋለው እንደሚገኝ አመልክተው፤ መብታቸውን የሚጠይቁትን ደግሞ እያስፈራራ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል በተለይም በመጠለያ ጣቢያዎች እየደረሰ ያለው አስከፊ ችግር ሕገ ወጥ ቡድኑ በሴራ የፈጠረው መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ ሕገ ወጥ ቡድን የተፈናቃዩቹ ችግር፣ሞትና ስቃይ እንዲቀጥል እያደረገ ነው ያሉት አቶ ጣዓመ፤ በተለይም ወደ ክልሉ የሚገባውን ሰብዓዊ እርዳታና ቁሳቁስ ለተረጂዎች በቀጥታ መድረሱን በተለያየ አካላት ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሕገ ወጥ ቡድኑ የሴራ ፖለቲካውን ለማራመድ ሲል በጭካኔ በትግራይ ችግር እንዲቀጥል እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
የፌዴራል መንግስት በመጠለያ ጣቢያዎች ለተፈናቃዮች እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።