በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል
ከሚሴ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
የ2018 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የንቅናቄ መድረክ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከሚሴ ከተማ እየካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፣ በክልሉ ሲከናወኑ በቆዩ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።
የተገኘውን ውጤት የበለጠ ለማስፋትም የህብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራም ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎችን ለማሳተፍ መታቀዱን ገልጸዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የበጋ ወራት 9 ሺህ 06 ተፋሰሶችን የሚያካልል 456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወንም አንስተዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ በበኩላቸው፣ በክልሉ በየአመቱ በሚከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የአፈር ለምነት ማሳደጉን፣ ምርታማነት መጨመሩን እንዲሁም የደን ሽፋንም እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የለሙ ተፋሰሶችም ለወጣቶች የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ረገድም ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡንም አስታውሰዋል።
የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው፣ በዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ሥራውን በማጠናከር ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዞኑ ዝናብ አጠር በመሆኑ የሚከናወነው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ስራ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።