ቀጥታ፡

በበጋ መስኖ ልማት ከራሳችን አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነናል-አርሶ አደሮች

ሀዋሳ፤ታህሳስ 19/2018 (ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን በበጋ መስኖ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ከራሳቸው አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ በበጋ መስኖ ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች እየለማ እንደሚገኝና 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ገጠር ልማት መምሪያ አስታውቋል።

በዞኑ ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ የጉድጓድ ውሀ በመጠቀም በመስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንዳሉት፥ በዓመት ሶስት ጊዜ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።

አርሶ አደር በርበራ ሌቲሞ በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ የጋሎ ኡርጌሳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ ቀደም ባሉት ዓመታት የመስኖ ልማት ስራዎች ላይ ተሳትፈው አያውቁም።

የበልግና የክረምት ዝናብን ጠብቀው ያለሙት የነበረው በቆሎ ከቤት ውስጥ ፍጆታ ያለፈ ጥቅም ሳያስገኝላቸው እሳቸውም ሳይለወጡ ዘመናትን ተሻግረዋል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመስኖ ልማት በመሳተፍ ባላቸው አንድ ሄክታር መሬት ላይ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያና ቲማቲም እያለሙ ይገኛሉ።

በሶስት ዙር ባለሙት የአትክልት ምርትም ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉና አምና ከጥቅል ጎመን ሽያጭ ብቻ 310 ሺህ ብር ማግኘት እንደቻሉ ይናገራሉ።

አሁን እያመረቷቸው ከሚገኙት የአትክልት ምርቶችም ከዚሀ ቀደሙ ከሚያገኙት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም አርሶአደሩ ገልጸዋል።

አርሶ አደር አጌርሶ ደበላ ደግሞ ከቀደሙት አርሶ አደር በተለየ ሁኔታ በመስኖ ስራ መሳተፍ ከጀመሩ አራት ዓመት ሆኗቸዋል።

ከመስኖ ልማት የሚገኘውን ጥቅም ቀደም ብለው የተረዱ አርሶ አደር ነበሩና ከሌላ ጎረቤታቸው ጋር በመሆን 22 ሄክታር መሬት በቃሪያ፣በጥቅል ጎመንና በቲማቲም ማልማታቸውን ይገልጻሉ።

''ከልማቱ የሚገኘውን ጥቅም ያወቀ አርሶ አደር መተኛት የለበትም'' የሚሉት አርሶ አደሩ በሄክታር እስከ 12 የጭነት አይሱዙ ሙሉ የቲማቲም ምርት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

አምና ካለሙት ቲማቲምና ጥቅል ጎመን 7 ሚሊዮን ብር እንዳገኙ የተናገሩት አርሶ አደሩ በዘንድሮ ዓመትም በእጥፍ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚጠብቁም ይናገራሉ።

የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ደሳለኝ እንዳሉት፥ በወረዳው አርሶ አደሩን በክላስተር በማደራጀት በበጋ መስኖ ስራ እንዲሳተፍ እየተደረገ ይገኛል።

በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ 174 የመስኖ ክላስተሮች እንዳሉ ገልጸው፥ አርሶ አደሮቹ ተመሳሳይ ምርት አምርተው ገበያ እንዳያጡ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያ፣ ሽንኩርትና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን በማሰባጠር እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዘው የበጋ ወቅትም ዘጠኝ ሺህ 720 ሄክታር መሬት በማልማት 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ወደ ስራ እንደተገባና በዚህም ከ14 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የዞኑ ገጠር ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዱሬሳ ሌዳሞ እንዳሉት፥ የውሀ አማራጭ ባለባቸው አካባቢዎች የወንዝና የጉድጓድ ውሀን በመጠቀም 35 ሺህ 254 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ እየለማ ይገኛል።

የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ከተረጂነት ለማውጣት የተያዘውን ግብ ለማሳካት በዞኑ ከ700 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የሚያስችሉ አምስት ጥልቅ ጉድጓዶችን በማዘጋጀት የመስኖ ልማት ስራው በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩ በግሉ አነስተኛ የውሀ ጉድጓድ እንዲያዘጋጅ በማድረግ 3 ሺህ 700 የውሀ መሳቢያ ሞተር በማሰራጨት ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እየለማ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

እየለማ ከሚገኘው መሬትም 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም