ቀጥታ፡

የመኸር ምርት ወደ ገበያ እየገባ መሆኑን ተከትሎ የምግብ እህል የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል - የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች

ወልዲያ፤ታህሳስ 19/2018( ኢዜአ)፡- በአሁኑ ወቅት የመኸር ምርት ወደ ገበያ እየገባ መሆኑን ተከትሎ የምግብ እህል የዋጋ ቅናሽ ማሳየቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች።

በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች የመኸር ምርት አሰባሰብ ሂደት እየተገባደደ ሲሆን ቀደም ብሎ የተሰበሰበው የሰብል ምርትም ለገበያ እየቀረበ ነው።

ኢዜአ ካነጋገራቸው የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ብዙነሽ ዓለሙ፣ የዘንድሮው የመኸር ምርት ተሰብስቦ ለገበያ መቅረብ በመጀመሩ የእህል ገበያው ቅናሽ እያሳየ ነው ብለዋል።

በዚህም 12 ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው የአንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ አሁን ላይ 10 ሺህ 500 እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰው ሰርገኛ ጤፍ ደግሞ ከ11 ሺህ ወደ 9 ሺህ 500 መቀነሱን ገልጸዋል።

የግብርና ምርትን ከአርሶ አደሩ በቀጥታ የሚገዙበት ሁኔታ በመመቻቸቱም ይበልጥ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አስማረች ምስጋናው፤ የመኸር ምርት ከመሰብሰቡ በፊት 8 ሺህ 500 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ማሽላ አሁን ላይ 7 ሺህ ብር መግዛታቸውን አንስተዋል። 

በአሁኑ ወቅት ግብይቱ በአብዛኛው ቀጥታ ከአርሶ አደሩ መሆኑን ገልጸው ይህም ህገወጥ ነጋዴዎችና ደላሎችን ለመከላከል ማገዙን ተናግረዋል።

የወልዲያ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ወንድሙ በበኩላቸው በመኸር አዝመራ የለማ ሰብል ተሰብስቦ ለገበያ እየቀረበ በመሆኑ የዋጋ መረጋጋት ታይቷል ብለዋል።

ምርቱ ሙሉ በሙሉ ተሰብስቦ ሲጠናቀቅ ገበያው ከአሁኑ በተሻለ እንደሚረጋጋ ይጠበቃል ያሉት ኃላፊው በአርሶ አደሩ እየቀረበ ያለው ምርት በቀጥታ ለሸማቹ የሚደርስበት ምቹ ሁኔታም ተፈጥሯል ብለዋል።

የወልዲያ ከተማ ህብረት ሰራ ማህበራት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንተነህ ሲሳይ፣ የከተማው ህብረት ስራ ማህበራት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚያስችል የጤፍ ግዥ እያከናወኑ ነው ብለዋል። 

እስካሁንም ከተለያዩ አካባቢዎች ጤፍ እየገዙ መሆኑን ጠቁመው ምርቱ በተመጣጠኝ ዋጋ ለሸማች እንደሚቀርብም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ማህበራቱ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ዱቄትና ሌሎች የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በመግዛት ለሸማቹ እያቀረቡ እንደሚገኙም አስረድተዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም