በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን ለማስፈን ሀገራዊ ምክክሩ ወርቃማ ዕድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን ለማስፈን ሀገራዊ ምክክሩ ወርቃማ ዕድል ነው
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 19/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን ለማስፈን የሀገራዊ ምክክሩ ያስገኘውን ወርቃማ ዕድል ሁሉም ዜጋ ሊጠቀምበት እንደሚገባ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የማደራጀትና ግብዓቶችን የማሰባሰብ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ማሳወቁ ይታወሳል።
የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን፤ ኢትዮጵያዊያን ምክክር በማድረግ በጋራ አጀንዳዎች ላይ መግባባት ባለመፍጠራቸው ሀገር ዋጋ ስትከፍል መቆየቷን ገልጸዋል።
በዚህም መነሻነት ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ በቆዩ ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ወርቃማ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያም በሃሳብ የበላይነት የተመሠረተ ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ ብሔራዊ መግባባትን ማጠናከር የሚያስችል የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓትና የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ሀገራዊ ምክክር አሳታፊ፣ አካታችና ተዓማኒነት ለማስጠበቅ በተከናወኑ የቅድመ ጉባኤ ምክክር ሂደቶች ላይ አዎንታዊ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ብሄራዊ መግባባትን ለማጠናከርና አንድነትን ለማጽናት ሀገራዊ ምክክር ትልቅ ዕድል መሆኑንም አመልክተዋል።
በቀጣይ ብሔራዊ መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የተፈጠረውን የሀገራዊ ምክክር ዕድል ሁሉም ዜጋ ሊጠቀምበት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የተርካንፊ ሰስተነብል ዴቨሎፕመንት መስራችና ዳይሬክተር ወርቅነሽ ቤጊ፤ በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ሂደት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ሴቶች በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር ሂደት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ብሔራዊ መግባባት የሚሹ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ተናግረዋል።
የዋይቡንቱ ዪዝ ፒስ ቢወልዲንግ አሊያንስ ፀሐፊ ሲሳይ ታረቀኝ፥ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር ሂደትም የወጣቶችን የነቃ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በቀጣይም ለዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።