ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለሕንድ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለሕንድ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር መፍጠሩን በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ለሕንድ አልሚ ባለሃብቶች ምቹ የልማት ከባቢ የፈጠረች ሀገር መሆኗንም በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች የተሰማሩ ሕንድ ባለሃብቶች ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካላቸው ሀገራት መካከል ሕንድ ከግንባር ቀደምቶቹ አንዷ ናት።

በዚህም የሕንድ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ትኩረት በሰጠቻቸው የጤና፣ የግብርና፣ ጨርቃ ጨርቅና ሌሎች መስኮች አምስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ ኢንቨስትመንት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በቀጣይም የሕንድ ባለሃብቶች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድል በመጠቀም በሥራ ዕድል ፈጠራና ምርታማነት ላይ በስፋት እንዲሳተፉ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

የሕንድ አልሚ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት ልማት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን በሥራ ዕድል ፈጠራና በዲጂታላይዜሽን የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሆነው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ለሕንድ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍሰት ምቹ ምኅዳር መፍጠሩን አብራርተዋል።


 

በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ከተሰማሩ የሕንድ አልሚዎች መካከል የሞሀን ግሩፕ ድርጅቶች ሥራ አስኪያጅ ሀርሽ ኮታሪ፤ የኢትዮ-ሕንድ የዳበረ ግንኙነት የኢንቨስትመንት አድማሳችን ለማስፋት ዕድል ፈጥሮልናል ብለዋል።

የኢትዮጵያና ሕንድ ታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት መሸጋገሩም የሕንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚኖራቸውን ዘርፈ ብዙ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ወሳኝ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የካዲላ ፋርማሲዩቲካል ኢትዮጵያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሬጂ ጆን፤ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሀገራቱን ስትራቴጂክ አጋርነት ለማጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። 


 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትና የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚክ ማሻሻያም የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር በማሳደግ የሕንድ ባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም