የአፍሪካ እግር ኳስ ኃያላኑ ኮትዲቯር እና ካሜሮን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ እግር ኳስ ኃያላኑ ኮትዲቯር እና ካሜሮን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2018(ኢዜአ)፦ የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ መርሃ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።
በዕለቱ የምድብ አምስት እና ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በምድብ ስድስት የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ኮትዲቭዋር ከአምስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ካሜሮን ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በማራካሽ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ኮትዲቭዋር ሞዛምቢክን፣ ካሜሮን ጋቦንን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
ሁለቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኃያላን በአህጉራዊው መድረክ ሲገናኙ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ ነው።
ሀገራቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ሱዳን እ.አ.አ በ1970 ባዘጋጀችው ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው። በወቅቱ ካሜሮን 3 ለ 2 አሸንፋለች።
እ.አ.አ በ1992 በሴኔጋል በተካሄደው 18ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜ ባደረጉት ጨዋታ ኮትዲቭዋር ካሜሮንን በመለያ ምት በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች። ኮትዲቭዋር በፍጻሜው ጋናን በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አንስታለች።
ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ በአህጉራዊው መድረክ የተገናኙት ኢኳቶሪያል ጊኒ እ.አ.አ በ2015 ባዘጋጀችው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው። በምድብ አራት በተደረገው ጨዋታ ኮትዲቭዋር በማክስ-አለን ግራዴል ጎል 1 ለ 0 አሸንፋለች።
በአጠቃላይ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫው አምስት ጊዜ ተገናኝተው ካሜሮን ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ ኮትዲቭዋር ሁለት ጊዜ ድል ቀንቷታል።
ኮትዲቭዋር የዘንድሮውን ጨምሮ ለ26ኛ ጊዜ እየተሳተፈች የምትገኝ ሲሆን ሁለት ጊዜ ዋንጫውን አንስታለች። የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ናት።
በአንጻሩ ለ22ኛ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫው የተሳተፈችው ካሜሮን አምስት ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ከግብጽ በመቀጠል ስኬታማዋ ሀገር ናት።
በአፍሪካ እግር ኳስ ደማቅ ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ሀገራት በጨዋታው ላይ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጨዋታውን የሚያሸንፈው ቡድን ወደ ጥሎ ማለፍ ይገባል።
በምድብ ስድስት ሌላኛው መርሃ ግብር ጋቦን ከሞዛምቢክ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 በአጋዲር ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ጨዋታ ካስተናገዱት ሽንፈት በኋላ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
በተያያዘም የምድብ አምስት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ አልጄሪያ ከቡርኪናፋሶ በሙላይ ኤል ሀሰን ስታዲየም ይጫወታሉ።
በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ አልጄሪያ ሱዳንን 3 ለ 0፣ ቡርኪናፋሶ ኢኳቶሪያል ጊኒን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።
በሌላኛው የምድቡ መርሃ ግብር ኢኳቶሪያል ጊኒ ከሱዳን ምሽት 12 ሰዓት ላይ በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን ይዟል።