ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ጥበብ የተሞላበት አመራር ውጤት ነው

አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 18 /2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ጥበብ የተሞላበት አመራር ውጤት መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች ታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ርስቱ ይርዳው በዚሁ ወቅት የህዳሴ ግድብ እውን የሆነው ጥበብ የተሞላበት አመራር በመሰጠቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በርካታ ፈተናዎችን በመቋቋም ዳግማዊ አድዋ የሆነውን የህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ያስመዘገበችው ድል የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ተግባር ምዕራፍ መሸጋገሩ የላቀ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።

ምንም እንኳ አንዳንድ አካላት አሁንም የግድቡን ፋይዳ በግልፅ ባለመረዳት የተለያዩ ፕሮፖጋንዳዎችን እያሰራጩ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን እራሷን ከድህነት ለማላቀቅ እና ዜጎቿ የተሻለ የኑሮ ዘይቤ እንዲኖራቸው በማለም ያላትን እምቅና ተፈጥሮአዊ ሀብት የመጠቀም መብትን መሰረት በማድረግ እንዲሁም ፈተናዎችን ድል በመንሳት ግድቡን እውን ማድረግ ችላለች ብለዋል።

አቶ ርስቱ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ አሻራ ያረፈበት መሆኑን በመግለፅ፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞችም በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አሁንም አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከተሰጠው ሀገራዊ ተልዕኮ በመነጨ ለግድቡ ደኅንነት የሚያደርገውን ክትትል እና ጥበቃ አጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በጉብኝቱ ተሳታፊ የነበሩ የአገልግሎቱ ከፍተኛ አመራሮች የህዳሴ ግድብን በቦታው ተገኝቶ መመልከት ልዩ ስሜትን ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል።

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ብዙ ተደክሞበታል የኢትዮጵያ ሕዝብም ጥሪት ነው ያሉት የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፤ በቀጣይም ግድቡ ያለምንም የፀጥታ ስጋት አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እና የሀገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የተቋሙ ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን ገልፀዋል።

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በመረጃ እና በደኅንነት ስምሪት ቀጣይነት ያላቸው ስራዎች እንደሚሰራም ከፍተኛ አመራሮቹ መግለጻቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ የላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም