የኢትዮጵያ እና ቻይና አጋርነት በተገነባበት ጠንካራ መሰረት ጸንቶ ይቀጥላል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ቻይና አጋርነት በተገነባበት ጠንካራ መሰረት ጸንቶ ይቀጥላል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ቻይና የረጅም ጊዜ አጋርነት በጠንካራ መሰረቱ ጸንቶ ይቀጥላል ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቡናን በቻይና ገበያ የበለጠ ለማስተዋወቅ እና ኤክስፖርቱን ለማሳደግ ያለመ ኮንፍረንስ በቻይና ሁናን ግዛት እየተካሄደ ነው።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ኮንፍረንሱን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ የኢትዮጵያ እና ቻይና አጋርነት ለረጅም ጊዜ ፀንቶ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ለዓለም በርካታ ባለልዩ ጣዕም ቡና ምርቶችን እያቀረበች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በስራ እድል ፈጠራ 25 በመቶ እና በውጭ ምንዛሬ 30 በመቶ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል።
ኮንፍረንሱ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ እና ቻይና ጠንካራ ግንኙነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው ወዳጅነታቸው በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት(all-weather strategic partnership) ምዕራፍ መሸጋገሩንም ነው ያወሱት።
ሁነቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካን ጥልቅ የኢኮኖሚ አቅም እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም(ፎካክ) አማካኝነት በግብርና፣ የገጠር አረንጓዴ ልማት ንግድና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ትስስር የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የአፍሪካ እና ቻይናን የንግድ ትብብር ዘላቂ እና ባለብዝሃ ዘርፍ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችንም አንስተዋል።
በቻይና ሁናን ግዛት ጁጆ ከተማ የኢትዮጵያ የቡና ስርጭት ማዕከል መከፈቱ ኢትዮጵያ በሰፊው የቻይና የቡና ገበያ ያላት ድርሻ እንዲያድግ የበኩሉን ሚና ይወጣል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
ከኢትዮጵያ የልማት ግቦች ጋር የተጣጣሙ የቻይና የኢንዱስትሪ ልማት ኢኒሼቲቮች በሌሎችም መስኮች ሊሰፋ እንደሚገባ ጠቁመው ይህም ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት በዓለም እሴት ሰንሰለት ውስጥ ድርሻቸው እንዲያድግ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አብራርተዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ ኮንፍረንሱ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትም አመስግነዋል።
በቻይና ሁናን ግዛት ጁጆ ከተማ በተዘጋጀው ኮንፍረንስ ከ700ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የኢትዮጵያን ባለልዩ ጣዕም ቡና ለማስቀመስ እቅድ ተይዟል።
ቻይና የኢትዮጵያ ቡና ዋና መዳረሻ እየሆነች የመጣች ሲሆን የዛሬ አምስት አመት የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ከነበረችበት 33ኛ ደረጃ በተያዘው አመት ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ብላለች።
ኮንፍረንሱ ቻይና በኢትዮጵያ ቡና ያላትን ተደራሽነት የበለጠ ለማሳደግና ወደ ቻይና የሚላከውን የቡና ኤክስፖርት መጠን ማሳደግ ያለመ መሆኑን ኢዜአ ከስፍራው ያገኘው ያመለክታል።