የመደመር መንግስት እሳቤን በመተግበር የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት እሳቤን በመተግበር የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል
ደብረ ማርቆስ/ገንዳ ውሃ/ወልዲያ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-የመደመር መንግስት እሳቤን በመተግበር የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።
በደብረ ማርቆስ፣ ገንዳ ውሃና በወልዲያ ከተሞች "የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል ሃሳብ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉባቸው የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር በተካሄደ መድረክ ላይ የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ እንደገለጹት፤ የመደመር መንግስት በወል ትርክት ላይ የተመሰረተ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት እየሰራ ነው።
ለዚህም የቀደመ መልካም እሴቶች ላይ ፈጠራና ፍጥነትን በማከል የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ግብ ተይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በመንገድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በሃይል አቅርቦትና ሌሎች መሰል መሰረተ ልማቶች ማተኮሩንም ገልጸዋል።
ከልማት ሥራዎች በተጓዳኝ በአካባቢው ሰላምን አጠናክሮ ለማስቀጠል ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ህዝብን በማሳተፍ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የአካባቢን ሀብት ለይቶ ማልማት ከተቻለ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል ትምህርት የተገኘባቸው ናቸው ብለዋል።
በመደመር መንግስት በልማትና በመልካም አስተዳደር የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ሥራዎች ይጠናከራሉ ያሉት ደግሞ በገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደ መድረክ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ ናቸው።
በዞኑ ያሉትን ፀጋዎች አልምቶ ለህዝብ ጥቅም ለማዋል ሰላምን ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ለዚህም በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም ሙሀመድ በበኩላቸው፤ በመደመር መንግስት እሳቤ በከተማዋ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተሰራ ነው።
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ በስኬት የተጠናቀቁ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የመንግስትን የልማት ቁርጠኝነት ያሳያሉ።
የመደመር መንግስት እሳቤዎችን ለማሳካት በሰላምና ልማት ግንባታ ላይ ህዝብን ያሳተፈ ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ናቸው።
ህዝቡም ሠላምና ልማትን የሚያደናቅፉ አካላትን በአደባባይ ጭምር ማውገዙን አስታውሰው ይህም ተጠናክሮ መጠቀል እንዳለበት አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ በአካባቢው የሰፈነው ሠላም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ አድርገዋል።
በየከተሞቹ በተካሄደ የውይይት መድረክ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።