ቀጥታ፡

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በእንስሳት ዘርፍ የተገኘው ስኬት ተጠናክሮ ይቀጥላል

ሀዋሳ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡- እንደ ሀገር በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር  የእንስሳት ዘርፍ ላይ የተገኘውን  ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል ለእንስሳት አያያዝና ጤና ትኩረት መሰጠቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። 

በግብርና ሚኒስቴር እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ የዶሮ ፣ የወተት ላሞችና የጥጆች አያያዝ እና ጤና አጠባበቅ ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ሥልጠና ለዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች በሀዋሳ ከተማ እየተሰጠ   ነው፡፡


 

በሥልጠናው መድረክ  የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፤ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በኢትዮጵያ የእንስሳት ቁጥርን መሠረት ካደረገ የተለመደ አሰራር በመውጣት ዘመናዊውን በመከተል ምርታማነትን ይበልጥ ማሳደግ እንዳስቻለ ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ በዝርያ ማሻሻል ፣ በግብአት አቅርቦት ፣ በምርትና ሌሎች ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ትላልቅ እመርታዎች መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

እንቁላል ፣ ወተትና ሌሎች የእንስሳት ተዋጽኦ  ምርቶች ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ በስፋት ወደ ገበያ የሚቀርብበትና  የዜጎችንም ገቢ ማሻሻሉን አንስተዋል፡፡

የወተት  ምርት በክልሎች ከአካባቢ ገበያ አልፎ ለአዲስ አበባ  እንዲሁም ለማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በስፋት እየቀረበ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን እንስሳት እና የመኖ አቅርቦትና እንክብካቤ በማድረግ እንዲሁም  ጤናቸውን በመጠበቅ ምርታማነትን ለማላቅ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የእንስሳት ጤና ፣ በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ዴስክ ኃላፊ  ሜሮን ሞገስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤   እንደ ሀገር የእንስሳት በሽታን መከላከል መሠረት ያደረገ የጤና አጠባበቅ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡


 

በሽታዎች ሲከሰቱ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዲያስችልም በየአካባቢው የእንስሳት ክሊኒኮች እንዲስፋፉ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ፡፡

በእንስሳት አያያዝና ጤና አጠባበቅ ላይ የተደራጀ መረጃ የያዙ መመሪያ ዶክመንቶች ለማስተግበር የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም አውስተዋል፡፡

በክልሉ እያደገ ባለው የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች ቁጥር ልክ የክትባትና ሌሎች የጤና አጠባበቅ ሥራዎች መሻሻላቸውን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ፎና ናቸው።  


 

በየቀበሌው አንድ የእንስሳት ጤና ኬላ እንዲሁም በሁሉም ወረዳዎች የእንስሳት ጤና ክሊኒኮችን የመገንባት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው  ላይ ከሲዳማ ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች  የተውጣጡ የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ  ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም