በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው
ወልቂጤ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በህዝብ ተሳትፎ የሚከናወኑ ትልልቅ የልማት ሥራዎች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና የብልጽግና ጉዞን የሚያፋጥኑ መሆናቸው ተገለጸ።
በክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ከቀቤና ልማት ማህበር ጋር በመተባበር ለሚገነቡት "ኢማም ሀሰን ኡንጀሞ ሆስፒታል" እና "ለፈትሁዲኒ ላሉተ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት" ማሰሪያ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ዛሬ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ለልማት ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ማስፈጸሚያ የሚውል ከ1 ቢሊዮን 700 ሺህ ብር በላይ ቃል ተገብቷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ መሃመድ ኑርዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በክልሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተከናወኑ ነው።
እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ የክልሉን የብልጽግና ጉዞ እንደሚያፋጥኑ ተናግረዋል።
ለአብነትም የቀቤና ልዩ ወረዳ ዘመናዊ ሆስፒታል እና አዳሪ ትምህርት ቤት የልማት ፕሮጀክቶች ባለቤትና ዋነኛ ተጠቃሚ ህዝብ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቶቹ ከመንግስት በተጨማሪ በህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚከናወኑ የተናገሩት መሃመድ (ዶ/ር) የክልሉ መንግስት ፕሮጀክቶቹ ስኬታማ እንዲሆኑ ድጋፉን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የቀቤና ልማት ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ ሙአዝ በድሩ (ዶ/ር)፤ የሚገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቶቹን በቴክኖሎጂ በማደራጀት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲያፈሩ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የሆስፒታሉ ግንባታም የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
በማህበረሰቡ ተሳትፎ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች የህዝብን ተጠቃሚነትና የወረዳውን ልማት የሚያጠናክሩ ናቸው ያሉት ደግሞ የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሃመድአሚን በደዊ ናቸው።
የሆስፒታሉ ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካባቢው ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት መደላድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
በተለይ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ እና ለሕክምና ወደ ሌሎች ከተሞች ይደረግ የነበረን ጉዞ ይቀንሳል ብለዋል።
በዛሬው እለትም ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ የሚሆን ከ1 ቢሊዮን 700 ሺህ ብር በላይ ብር ቃል መገባቱን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ግንባታ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለሚገነቡ የሕክምና እና የትምህርት ፕሮጀክቶች የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ለይላ ነጋሽ የተባሉ የልዩ ወረዳው ነዋሪ ናቸው።
ለእነዚህ ልማቶች ከግብርና ሥራቸው በሚያገኙት ገቢ ብር 500 ሺህ ለመለገስ ቃል መግባታቸውን ገልፀዋል ።
አቶ መሃመድ ሀሰን የተባሉ ነዋሪም ለአዳሪ ተምህርት ቤቱና እና ለሆስፒታሉ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና የአካባቢው ተወላጆች ተገኝተዋል።