ቀጥታ፡

የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርቶችን በስፋት እንዲያቀርቡ በግብአትና ምርምር እየታገዙ ነው

ባሕር ዳር ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርቶችን በስፋት ማቅረብ  እንዲችሉ  በበቂ ግብዓትና ምርምር እየታገዙ መሆኑ ተገለጸ። 

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ የቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዘርፉ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ዛሬ አካሄዷል።


 

በአውደ ጥናቱ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ሳምሶን አሰፋ እንደተናገሩት፤ ለሃገር ውስጥ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች  ጥራቱን የጠበቀ በቂ የጥጥ ምርት እየቀረበ ነው።

በዚህም ባለሃብቶችን በዘርፉ የማሰማራትና የአርሶ አደሮችን ምርታማነት በማሳደግ የጥጥ ምርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትብብር እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም በምርምር ከማገዝ ባለፈ ምርጥ ዘር የማቅረብና ሌሎች ግብዓቶችን የማሟላት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በጥጥ የሚለማው መሬት ባለፉት አምስት ዓመታት እያደገ መምጣቱን አንስተው፤ ባለፈው የመኽር ወቅትም 110 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ መልማቱን አብራርተዋል።


 

ለዘርፉ ኢንዱስትሪዎች በቂ ጥጥ ከማቅረብ ባሻገር ባለፈው ዓመት ከፍጆታ የተረፈውን ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለም አውስተዋል።

የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠልም ዘርፉን በምርምር ለማገዝ ኢንዱስትሪዎችን፣ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማትን ያካተተ ብሄራዊ ፎረም ተዋቅሮ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ የቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የቴክስታይል ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዘርፉን ለማዘመን በበቂ መጠን የሰለጠነ የሰው ሃይል ከማፍራት ባለፈ ለጥናትና ምርምር ስራዎች ሰፊ እገዛ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በሃገሪቱ ከሚገኙ 114 ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር  በምርት ብዛትና ጥራት ተፎካካሪ እንዲሆኑ እገዛ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። 

ተኪ ምርትን በሃገር ውስጥ ማምረት መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ላቦራቶሪዎችን በማደረጀት፣ የራሱን ፋብሪካ በማቋቋም፣ ተማሪዎችን በማስተማርና የምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ  ይገኛል ብለዋል።

የዛሬው አውደ ጥናትም ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ፤ የቴክስታይል ዘርፉን ለማዘመን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የግብርናው ዘርፍና ኢንዱስትሪዎች በትስስር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።


 

ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርበው የጥጥ ምርት ጥራቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት አንስተው፤ ለዚህም በምርምር የታገዘ ስራን ማጠናከር ተገቢ እንደሆነም አንስተዋል።

በአውደ ጥናቱ ከፌደራል ተቋማት፣ ከኢንስቲትዩቱና ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ የዘርፉ ምሁራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም