ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ታሪክ መልኮችና ሂደቶች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ አሻራ አሳርፏል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በተጓዘችባቸው የዘመናዊ ታሪክ መልኮችና ሂደቶች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ አሻራ ማሳረፉን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የቀድሞ ተማሪዎች የቤተሰብ ቀን እየተከበረ ነው።

በመርኃ-ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የዛሬዎቹ አንጋፋ ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ታሪክ ሂደት ጉልህ አሻራ ያለው ነው፡፡

በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና፣ በኪነጥበብ እና ሌሎችም ዘርፎች ከተመዘገቡ ስኬቶች ጀርባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አበርክቶ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውጤት በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው በመግለጽ፤ ለዜጎች የተመቸችና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚጥሩ ምሁራንን አፍርቷል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያውያንን የአኗኗር ሁኔታ የሚያዘመኑ የምርምር ሥራዎችና የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል፡፡

መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነፃና ገለልተኛ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የመማር ማስተማር የሚካሄድባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራሱን አስተዳደር፣ ገቢና የዕውቀት መንገድ ይዞ መሄድ የሚችልበት የራስ ገዝነት አስተዳደር ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያገኘው የአካዳሚክ ነጻነት ሃላፊነት የሚሰጥ ጭምር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ያገኘውን እድል በመጠቀመ ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ትልቅ ትቋም መሆን እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከ75 ዓመት በፊት በ50 ተማሪዎች ማስተማርን አሀዱ ብሎ የጀመረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጉዞው 300 ሺህ ተማሪዎችን አስመርቋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሻራ በሁሉም ዘርፍ ይታያል ያሉት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ፤ በጥናትና ምርምር ሀገር አሻግረዋል በማስተማር ትውልድ ቀርጸዋል ብለዋል።

ሀገር በመምራት ለውጥ አምጥተዋል፣ የንግድ ተቋማትን መርተው ባለጸጋ ሆነዋል፣ በሕክምና ተሰማርተው ሚሊዮኖችን ፈውሰዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ በመወከል ብሔራዊ ጥቅሟን ያስከበሩ ዲፕሎማቶችን መፍጠሩንም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በኢትዮጵያ ለውጥ ታላቅ አሻራ አኑረዋል ያሉት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ፤ በዓለም ገናና ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም