ቀጥታ፡

በክልሉ ከ78 ሺህ በላይ የቤተሰብ መሪዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ተሸጋግረዋል

ዲላ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ5ኛ ዙር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በተደረገላቸው ድጋፍ ከ78 ሺህ በላይ የቤተሰብ መሪዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገራቸውን የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

በጌዴኦ ዞን በአምስተኛ ዙር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የተሸጋገሩ 6ሺህ 111 የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ዛሬ በዲላ ከተማ ተመርቀዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሽፈራው ቦጋለ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በልማታዊ ሴፍቲኔት ለታቀፉ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ ነው።


 

በአምስተኛ ዙር የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በተደረገላቸው ድጋፍ ከ78 ሺህ በላይ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ከተረጂነት ተላቀው ራሳቸውን በመቻል ወደ ምርታማነት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ የተመረቁ የቤተሰብ መሪዎችም ትጋታቸውን በመቀጠል ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች መትረፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በዞኑ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተግባራዊ ከተደረገ ጊዜ አንስቶ በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ ናቸው።


 

ይህም በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ ዜጎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ተሸጋግረው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።

የዛሬ ተመራቂዎችም በፕሮግራሙ ድጋፍ ያገኙትን ክህሎትና ያካበቱትን ሃብት አቀናጅተው ለበለጠ ውጤት መትጋት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

የጌዴኦ ዞን አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ተድላ ጌታሁን በበኩላቸው፤ ዛሬ ከተረጂነት ተላቀው የተመረቁ 6 ሺህ 111 የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች በዞኑ አራት ወረዳዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደነበሩ አስታውሰዋል።


 

በተለይ በሌማት ትርፋት፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በእንስሳት እርባታና ሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸው መረጋገጡን አንስተዋል።

በዚህም በርካቶች ለራሳቸው ቋሚ ገቢና ሥራ ከመፍጠር ባለፈ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ችግራቸውን መፍታት እንደቻሉ አስረድተዋል።

ከተጠቃሚዎች መካከል የወናጎ ወረዳ ነዋሪ አቶ ማቲዎስ ሌጌ፤ በተደረገላቸው ድጋፍ ኑሯቸውን መቀየሩን አንስተዋል።


 

በንብ ማነብና በእንስሳት እርባታ ዘርፎች መሰማራታቸውን ጠቅሰው በተለይ ለገበያ ከሚያቀርቡት የማር ምርት ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ተቀማጭ ካፒታላቸው ከ200 ሺህ በላይ መድረሱን አንስተው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም