በአማራ ክልል የ30 ቅርሶች ጥገና እና የ11 ሙዚየሞች የግንባታ ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የ30 ቅርሶች ጥገና እና የ11 ሙዚየሞች የግንባታ ስራ እየተከናወነ ነው
ባህርዳር ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ የ30 ቅርሶች ጥገና እና የ11 ሙዚየሞች የግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የቅርስ ጥገና እና የሙዚየም ግንባታ ስራን በማስመልከት ቢሮው ከቅርስ ባለቤቶችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በባህርዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ፤ በክልሉ የቱሪዝም ሃብቶችን የማልማትና የመጠበቅ እንዲሁም የማስተዋወቅ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በያዝነው በጀት ዓመት የክልሉ መንግስት በመደበው 111 ሚሊዮን ብር የ30 ቅርሶች ጥገና እና የ11 ሙዚየሞች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የጥንታዊ ቅርሶች ጥገና እና የሙዚየም ግንባታ ስራዎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በሰሜን ጎንደር ዞን የፅርሃ ፅዮን ቅድስት ደረስጌ ማርያም ቤተክርስቲያን ገዳም አስተዳዳሪ መምህር ቆሞስ አባ ተከስተ ብርሃን ከውነው፤ ቤተክርስቲያኗ በውስጧ በርካታ ቅርሶች እንዳሉ ጠቅሰው ከክልሉ መንግስት በተመደበ በጀት እየተገነባ ያለው ሙዚየም ቅርሶቹን በተመቸ ቦታ በማስቀመጥ ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የመርጡ ለማርያም ገዳም የሙዚየም ግንባታ ኮሚቴ አባል አቶ ተመስገን አባቡ በበኩላቸው፤ በጥንታዊ ገዳሙ በርካታ ጥንታዊ ተንቀሳቃሽና ቋሚ የቅርስ ክምችት ስለመኖሩ አንስተዋል።
የነገስታት ዘውዶች፣ በርካታ የብራና መፃህፍትና ሌሎች የጥንት ንዋየ ቅድሳት እንደሚገኙ ጠቁመው ቅርሶቹን ለመጠበቅም ባለ 3 ወለል የሙዚየም ህንፃ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ቅርስ ጠባቂዎች፣ የቅርስ ጥገና ቁጥጥርና አሰሪ ኮሚቴዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።