ቀጥታ፡

በክልሉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ወላይታ ሶዶ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አምራቹንና ሸማቹን በማገናኘት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።

የክልሉ ሕብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ከክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሕብረት ሥራ ማህበራት የንቅናቄ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።

"ጠንካራ የቁጠባና ሕብረት ሥራ ማህበራት ለምግብ ዋስትና እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ" በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የንቅናቄ መድረክ ላይ የክልሉ የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ፤ በክልሉ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እየቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በተለይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት በማቅረብ አምራቹና ሸማቹን በማገናኘት ገበያን ለማረጋጋት በሚሰራው ሥራ  የሕብረት ሥራ ማህበራት ድርሻ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም የሕብረት ሥራ ማህበራትን አቅም በማጎልበት በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማሳደግና ህገ ወጥ ደላሎችን ከገበያ ለማስወጣት በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።

በየአካባቢው አምራቹንና ሸማቹን በማገናኘት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ውጤት እያስገኝ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም መተግበሩን ተከትሎ ሕብረት ሥራ ማህበራት ተወዳዳሪና ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመው፣ ሁሉም ዜጋ በነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ እንዲወዳደር መስራት ይገባል ብለዋል።

ከሀገራዊ ለውጥ ወዲህ የኅብረት ሥራ ማህበራት ያሉባቸውን ተግዳሮቶች በመፍታት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የአሰራር ሥርአት መዘርጋቱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ፎላ ናቸው።


 

በክልሉ 2 ነጥብ 57 ቢሊዮን ካፒታል ያፈሩ 6 ሺህ 381 መሰረታዊና 30 የህብረት ሥራ ዩኒዬኖች እንዳሉ ጠቁመው በእነዚህም 1 ሚሊዮን 178 ሺህ በላይ አባላት ታቅፈው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ማህበራቱ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በማሰራጨትና የፋይናንስ ትስስር በመፍጠር አባላቱ በገቢ ማስገኛ ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻላቸውንም ጠቁመዋል። 

ለአብነትም ወጣቶችና ሴቶች በእንስሳት ልማትና በእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ላይ በመሰማራት ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎችም የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የሕብረት ሥራ ሪፎሪም ትግበራ ከተጀመረ ወዲህ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን በማቅረብ ገበያ እያረጋጉ እንደሚገኙም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፤ የሕብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም ማስጀመሪያ ንቅናቄ በማድረግ ወደ ሙሉ ትግበራ ከተገባ ወዲህ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል። 

ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ባለድርሻ አካላት ተግተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም