ቀጥታ፡

የማዕድን ሃብትን  እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

አሶሳ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-የማዕድን ሃብትን በጥናትና ምርምር በመታገዝና እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የእምነበረድ እና ግራናይት ምርታማነትን በማሳደግ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ፕሮጀክት አስጀምሯል።


 

ምርምሩ እምነበረድ፣ ግራናይት እና ሌሎች ማዕድናት በአግባቡ ተዘጋጅተው እና እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የማዕድን ኢንዲስትሪ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብስራት ከበደ (ዶ/ር)፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የማዕድን ዘርፍ የሀገርን ኢኮኖሚ እንዲደግፍ ብዙ እየተሰራበት መሆኑን አንስተው በዚህም ውጤት መጥቷል ብለዋል።

በሁሉም አካባቢዎች ማዕድን በስፋት እየተመረተ እና ለብዙዎች የስራ አድል እየፈጠረ ከመሆኑም በላይ የሀገርን የምጣኔ ሃብት እድገት እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የማዕድን ሃብትን በጥናትና ምርምር በመታገዝና እሴት በመጨመር ከሀገር ወስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ በብዛትና በአይነት ለማቅረብ የሚያስችል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ የሚያደርጉት ምርምር የማዕድን ሀብትን ከብክነት እና ብክለት መታደግ የሚያስችልና የዘርፉን ልማት የሚያሳድግ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

የማዕድን ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ አምስት ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑን ጠቁመው ለአብነትም የድንጋይ ከሰል ምርት ወደ ውጪ መላክ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የማዕድን ዘርፉን ለማልማት እያደረገ ያለው ጥናትና ምርምር ስራ ውጤታማ እንዲሆን ኢንስትቲዩቱ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ከማል አብዱራሂም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የማዕድን ዘርፉ በምርምር እና ቴክኖሎጂ ታግዞ የተፈለገውን ሀገራዊ ጥቅም እንዲሰጥ የማድረግ ጥረት ይቀጥላል ብለዋል።

በቅርቡም የእምነበረድ ማሰልጠኛ ማዕከል በመክፈት ምርቱ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲዘጋጅ እና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በእምነበረድ እና ግራናይት አመራረት እና አጠቃቀም ላይ የሚያደርገው ጥናትና ምርምር ማዕድናቱ በሚፈለገው ቅርጽ ተዘጋጅተው የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ የሚያግዝ እንደሆነ አብራርተዋል።

በመድረኩ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የማዕድን ዘርፍ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም