ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ምርታማነትን በማሳደግ ለገበያ መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018 (ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለገበያ መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የተለያዩ ከተማ ከንቲባዎች ገለጹ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው  ከንቲባዎች እንደገለጹት በከተሞች  የሌማት ትሩፋት፣ የከተማ ግብርና እና ሌሎች ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች በስፋት ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ። 

እነዚህ ንቅናቄዎች ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከንቲባዎቹ አክለውም አምራቾችና ሸማቾች በቀጥታ የሚገናኙባቸውን የገበያ አማራጮች በማስፋፋትና ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም አንስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የከተሞችን የገቢ ምህዳር ለማስፋትና የመሰብሰብ አቅምን ለማሳደግ ግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ያሳተፈ የንቅናቄና የሕግ ማስከበር ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑ ገልጸዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሩድ ከድር በከተማቸው አምራችና ሸማች በቀጥታ የሚገናኙባቸው ገበያዎች በመስፋፋታቸው ሸማቹ ማህበረሰብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል። 

ኢኮኖሚው ያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ ሀገራዊ እቅዶችን ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ከንቲባው አረጋግጠዋል።

የከሚሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሸሪፍ ቃሲም በበኩላቸው በከተማቸው በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በአሳ፣ በእንስሳትና በንብ እርባታ ዘርፎች በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። 

ይህም ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለገበያ መረጋጋት የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጉን ለአብነት ጠቅሰው፤ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትን ለመገንባትም ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የቦዲቲ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ  አይናለም በለጠ በበኩላቸው የሌማት ትሩፋትና የሰንበት ገበያዎች የኑሮ ውድነቱን በማቃለልና ገበያውን በማረጋጋት ረገድ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆኑን ተናግረዋል። 

የከተማዋን ገቢ ለማሳደግም የገቢ አማራጮችን የማስፋትና የንግድ ሥርዓቱን የማዘመን ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም