በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚንጸባረቁ የኢትዮጵያዊነት ውብ ህብረ-ቀለማት አንድነትን፣ ትብብርንና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚንጸባረቁ የኢትዮጵያዊነት ውብ ህብረ-ቀለማት አንድነትን፣ ትብብርንና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚንጸባረቁ የኢትዮጵያዊነት ውብ ህብረ-ቀለማት አንድነትን፣ ትብብርንና አብሮነትን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የቀድሞ ተማሪዎች የቤተሰብ ቀን እየተከበረ ነው።
በመርኃ-ግብሩ ላይ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የዛሬዎቹ አንጋፋ ምሁራን፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ውብ ህብረ-ቀለም ይንጸባረቃል።
በዩኒቨርሲቲ የሚንጸባረቁ የኢትዮጵያዊነት ውብ ህብረ-ቀለማት አንድነትን፣ ትብብርንና አብሮነትን እንደሚያጠናክር ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በራስ ገዝነት ሂደት ወደ ፊት የሚያሻግሩ የለውጥ ስራዎች የተጀመሩበት ወቅት መሆኑን አንስተዋል።
በዘንድሮው ዓመት በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ያበረከተውን አስተዋጽኦ የሚዘክርበትና አሻራውን የሚያሳይበት 75ኛ ዓመት በዓሉን እያከበረ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አቅጣጫ የተለሙና እየተለሙ ያሉ ዕውቅ ምሁራንን ያፈራ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዓለም ስመ-ጥር ምሁራንን ያፈራው በአንጋፋነቱ ብቻ ሳይሆን በአስተዳደር ብቃቱ ጭምር መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች የቤተሰብ ቀንም የጋራ ቤታችንን በማደስ በወደፊት አቅጣጫው ላይ አሻራችንን ማስቀመጥ ያግዛል ብለዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያዊነትን ያወቅንበት ትልቅ የህይወት ምዕራፍ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለዛሬ ማንነታችን መሰረት የጣሉ አስደናቂ የሀገር ባለውለታ መምህራን ቁርጠኝነት የጎላ እንደነበር ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዙ የሚያሳልጡ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባው ገልጸው፤ ለዚህም ሁላችንም መደገፍ አለብን ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከ75 ዓመት በፊት በ50 ተማሪዎች ማስተማርን አሀዱ ብሎ የጀመረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ75 ዓመት ጉዞው 300 ሺህ ተማሪዎችን አስመርቋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሻራ በሁሉም ዘርፍ ይታያል ያሉት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ፤ በጥናትና ምርምር ሀገር አሻግረዋል በማስተማር ትውልድ ቀርጸዋል ብለዋል።
ሀገር በመምራት ለውጥ አምጥተዋል፣ የንግድ ተቋማትን መርተው ባለጸጋ ሆነዋል፣ በሕክምና ተሰማርተው ሚሊዮኖችን ፈውሰዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ በመወከል ብሔራዊ ጥቅሟን ያስከበሩ ዲፕሎማቶችን መፍጠሩንም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በኢትዮጵያ ለውጥ ታላቅ አሻራ አኑረዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በዓለም ገናና ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ በጋራ እንስራ የሚል ጥሪም አስተላልፈዋል።