ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን- የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን- የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች
ባህርዳር ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በመንግስት እየተደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በከተማ አስተዳደሩ ሁሉም ክፍለ ከተሞች "የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል።
በውይይት መድረኮቹ በተለይም ለሰላም ጉዳይ መንግስት በሁሉም አካባቢዎች እያደረገ ያለውን ጥረት አንስተው ታጣቂዎችም የሰላምን ጥሪ በመቀበል ወደ ውይይት መምጣት አለባቸው ብለዋል።
በዚህ ሂደት የመንግስትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እና ይህንኑ ተከትለው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን አመስግነው ቀሪዎችም ጊዜ ሳያባክኑ እንዲመጡ ጠይቀዋል።
የሰላምና የልማት ጉዳይ የጋራ አጀንዳ በመሆኑ ሁላችንም የመንግስትን ጥረት በማገዝ ለዘላቂ ሰላም በጋራ እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በከተማዋ በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ የውይይት መድረኩን የመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ብረሃን ንጉሴ፤ በከተማዋ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የኮሪደር ልማት፣ ሰፋፊ የአስፋልት መንገዶች፣ የሌማት ትሩፋት፣ የስማርት ሲቲና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የበጋ መስኖ ልማት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የሌማት ትሩፋትና ሌሎችም የግብርና ስራዎች የሚቀጥሉ ስለመሆኑም አረጋግጠዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካን ጨምሮ በርካታ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በመንግስት ተወጥነው እየተሰሩ መሆኑን አንስተው የሀገርን ብልጽግና የማረጋገጥ ስራ ትኩረት የተሰጠው ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።
በዚህ የልማት ጥረት ውስጥ ሰላም መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው በዚህ ረገድ የህዝቡ ትብብር፣ እገዛና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደት የህዝቡን የሰላምና የልማት ጥረት አድንቀው በቀጣይ መተጠናከረ መልኩ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።