ኢንተርፕራይዞች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንተርፕራይዞች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ይገኛሉ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ይገኛሉ ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለፁ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ በይፋ ተከፍቷል።
ባዛሩ "ድምቅ በኢትዮጵያ ምርት" በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ታህሳሥ 18 እስከ ነገ ታህሳሥ 19/2018 ዓ.ም ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን በባዛሩ ላይ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን አቅርበዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት መሠረትና የጀርባ አጥንት ናቸው።
ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ይገኛሉ ሲሉም ተናግረዋል።
መንግሥት የዘርፉን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በመረዳት ይበልጥ ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለው ሚና የጎላ እንዲሆን የሚያስችል ምቹ መዋቅራዊ ሥርዓት መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡
የዛሬው ኤግዚቢሽንና ባዛርም የዚሁ አካል መሆኑን አንተው ባዛሩ አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማች ማህበረሰብ በማቅረብ የገበያ አድማሳቸውን እንዲያሰፉ ያስችላቸዋል ብለዋል።