ቀጥታ፡

የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት የወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያ ችግር የፈታ ነው

ጎንደር ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት ከውበት ባሻገር የወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያ ችግር የፈታ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።

የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት የእግረኛና የብስክሌትመንገዶችን እንዲሁም የአረንጓዴ ልማትና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን በማካተት ደረጃውን ጠብቆ በጥራትና በፍጥነት የተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

በከተማዋ የዓለም ቅርስና የሀገር ሃብት ሆኖ የሚገኘው የአጼ ፋሲል ቤተመንግስትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት እድሳት ተደርጎለት ተመርቆ የከተማዋ ተጨማሪ ውበት ሆኖ ለጎብኝዎች ክፍት ተደርጓል። 

የአጼ ፋሲል ቤተመንግስት እድሳት ታሪክን በመጠበቅ ይበልጥ ውብና ማራኪ አካባቢ እንዲኖረው የተደረገ ሲሆን ቅርሱን በኮሪደር ልማት ከከተማዋ ጋር በማሰናሰል ለጎብኝዎች ምቹና ተመራጭ ከተማ ማድረግ ተችሏል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግስት የከተሞች ልማት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት በማዘመን ለነዋሪዎች፣ ለጎብኝዎችና ለኢንቨስትመንት የተመቹ በማድረግ የሚታዩ አስደናቂ ተግባራትን አከናውኗል።

የከተሞች ልማት ሲነሳ ጎንደር ተጠቃሽ መሆኗን የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት ከውበትም ባሻገር የወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያ ችግር የፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታን በመጠቀም ደረጃቸውን የጠበቁ አራት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ግንባታን ጨምሮ የፋሲለደስ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ እድሳት ስራ እንዲከናወን በር ከፍቷል ብለዋል። 


 

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ የማስ ስፖርት፣ የሜዳ ቴኒስ፣ የቅርጫት ኳስና የእግር ኳስ ጨዋታ፣ ልምምድና ውድድር ለማካሄድ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የስታዲየሙ እድሳት ስራ የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ክለብ  በራሱ ሜዳ ልምምዶችና ውድድሮችን እንዲያካሂድ በማስቻል የከተማውን የስፖርት ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አንተነህ ገብረሚካኤል፤ የኮሪደር ልማቱ በተለይም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ችግርን የፈታ በመሆኑ ተደስተናል ብሏል።


 

የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ሄለን ሀብቴ፤  ከተማ አስተዳደሩ በሚያካሂደው የኮሪደር ልማት ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የሰጠው ልዩ ትኩረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግራለች። 


 

በአእምሮና በአካል የዳበረና ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ለማፍራት ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት የጎላ ሚና እንዳላቸው ጠቁማለች፡፡ 

በ2ኛው ምእራፍ የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ልማት እየተከናወነ ሲሆን የአስፋልት መንገድ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ የመዝናኛ ስፍራዎችና ሌሎችም የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም