ቀጥታ፡

የበጋ መስኖ ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያሳደገ ነው- አርሶ አደሮች

ወልቂጤ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በበጋ መስኖ ልማት ሥራ የምግብ ዋስትናችንን ከማረጋገጥ ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችንን እያሳደግን ነው ሲሉ የጉራጌ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የአበሽጌ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጅላሉ አብዶ በመስኖ ልማት አራት ተኩል ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎችና አትክልት እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመስኖ ልማት ሥራ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ከምርት ሽያጩ ገቢ በማግኘት ሃብት እያፈሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ባለፈው ዓመት ከሽንኩርት ሽያጭ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ አግኝቻለሁ ብለዋል።


 

ከአራት ሔክታር በሚበልጥ መሬት በበጋ መስኖ ልማት ሰብልና አትክልት እያለሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የአበሽጌ ወረዳ አርሶ አደር መላኩ ቢረዳ ናቸው።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ይበልጥ ትኩረት በተሰጠው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በመሳተፍ ገቢያቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል።

የቸሃ ወረዳ አርሶ አደር ዳንኤል ሺፈታ በበኩላቸው፤ ከከፍተኛ ትምህርት ተመርቀው ሥራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ በመስኖ ልማት መሰማራትን እንደመረጡ አስታውቀዋል።

በበጋ መስኖ አትክልት፣ ፍራፍሬና ስንዴ እያለሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከቤተሰብ መሬት በተጨማሪ መንግሥት ባመቻቸላቸው ሰባት ሔክታር ላይ ስኬታማ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል።

ቀደምሲል ዝናብ ጠብቀው በዓመት አንድ ጊዜ ያመርቱ የነበሩ አርሶ ደሮች አሁን አራት ጊዜ እስከማምረት መድረሳቸውንም አንስተዋል።

በዞኑ የገጠርና የከተማ የግብርና ኢንሼቲቭን ለማሳካት በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ያመላከቱት ደግሞ የጉራጌ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አበራ ወንድሙ ናቸው።


 

ለእርሻ የሚሆኑ ሁሉንም መሬቶች በማልማት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ውጤት እየተገኘ መምጣቱንም አስረድተዋል።

በዞኑ በበጋ መስኖ 26 ሺህ 872 ሔክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ በተሠራው ሥራ እስካሁን ከ21 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት መልማቱን ጠቁመዋል።

ለውጤታማነቱ የአመራሩና የባለሙያው ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው፤ የግብዓት እጥረት መፈታቱና የአርሶ አደሩ ግንዛቤ እያደገ መምጣቱ የመስኖ ልማቱን ስኬታማ እንዳደረገው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም