ልማት እንዲፋጠን ክትትልና ድጋፋችንን እናጠናክራለን- የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ልማት እንዲፋጠን ክትትልና ድጋፋችንን እናጠናክራለን- የምክር ቤት አባላት
ባሕርዳር ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ሰላምን በማጽናት ልማት እንዲፋጠን ክትትልና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ከሰሜን ጎንደር ዞን ድልይብዛ ምርጫ ክልል የተወከሉት አቶ ብርሃኑ ዘውዱ ፤ በክልሉ ሰላምን ለማዝለቅ የሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎና ድጋፍ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
ችግር በውይይት እንጂ በግጭት እንደማይፈታ በመገንዘብ የቀሩ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ ተከትለው እንዲመለሱ መክረዋል።
የክልሉን ሰላም በማዝለቅ ልማቱ ይበልጥ እንዲፋጠን ክትትልና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ከደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ምርጫ ክልል በምክር ቤቱ የተወከሉት ወይዘሮ ፋጡማ ይማም በበኩላቸው፤ ሰላምን ለማዝለቅ የምክር ቤት አባላት ድርብ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
አሁን በክልሉ የሰፈነውን ሰላም ለማዝለቅ ከሕዝቡ ጋር በመሆን ድጋፍና ክትትላቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል አቶ አሰፋ ይመር፤ የሰላም አማራጭን ተከትለው የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች እንደሚበረታቱና ይህም ሰላምን ለማፅናት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የቀሩ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ የተጀመረውን ስራ ለማጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡