ውድድሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ማህበራዊ ትስስር ለማጎልበት ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
ውድድሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ማህበራዊ ትስስር ለማጎልበት ያግዛል
ነቀምቴ ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ በተካሄደው ስፖርት ለሰላም ውድድር የከተማዋ ነዋሪዎች ማህበራዊ ትስስራቸውን ለማጎልበት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለጸ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር አስተባባሪነት የስፖርት ለሰላም የሩጫ ውድድር ዛሬ በነቀምቴ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ማርቆስ ገነቲ፣ የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ወጋሪ ነገራ፣ የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሰረት ሀይሉ ፣ የወለጋ ዩኒቨርስቲ መምህራን እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ሩጫውን ያስጀመረው የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ማርቆስ ገነቲ ባስተላለፈው መልዕክት፤ የሰላም ሩጫው የተካሄደው ሰላምን ለማፅናት በሚደረገው ጥረት የሕብረተሰቡን የጎላ ተሳትፎ ለማስገንዘብ ነው ብሏል።
በሰላም ሩጫውም ነዋሪዎቹ ሰላምን ጠብቆ ለማዝለቅ፣ ልማትን ለማስቀጠልና ማህበራዊ ትስስራቸውን ለማጎልበት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግሯል።
የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሰረት ሀይሉ በበኩላቸው፤ አስተዳደሩ የሕግ የበላይነት በማስከበር ሰላምን በማፅናት የሕብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት አበክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ የተካሄደው የሰላም ሩጫም በአካባቢው ያለውን ሰላምና ልማትን አጉልቶ ያንጸባረቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማዋ በፈጣን የእድገት ጎዳና ላይ ናት ያሉት ከንቲባው፤ ይህንን እውነታ ለማሳየት የሰላም ሩጫው የማይተካ ድርሻ አለው ብለዋል።
የነቀምቴ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በሰላም ሩጫው በመሳተፍ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት ልማትና ሰላምን ለማፅናት ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋፍ ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
10 ኪሎ ሜትር በሸፈነው ሩጫ ላይ የተሳተፈችው ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ሳጅን አትሌት ጉተኒ ሻንቆ ፤ በወለጋ አካባቢ ያለውን ሰላምና ልማት በማድነቅ የሚበረታታ መሆኑን ተናግራለች።
ዛሬ የተካሄደው ስፖርታዊ ውድድር የአካባቢውን ትክክለኛ ገጽታ ለማሳየት እንደሚያግዝም ጠቁማለች።