የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል
አክሱም፤ ታህሳስ 18/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ በአክሱም ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን በውል ባልታወቀ ምክንያት እንዲታጣ ተደርጓል።
የባህር በር ማጣት የብዙዎች ቁጭት ሆኖ ቆይቶ አሁን ላይ የትውልድ ጥያቄና የሀገር የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ግልጽ የሆኑ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን የሀገሪቱ የምጣኔ ሃብት እድገትና የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ የታሪክና የህግ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከመሰረታዊ አገልግሎቱ ባለፈ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል መምህር በረከት ሀይለ፤ ኢትዮጵያ ግዙፍ ኢኮኖሚ እና ብዙ ህዝብ ይዛ የባህር በር ልታጣ አይገባም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በቅርብ ርቀት ላይ እያለች ሌሎች ከሩቅ መጥተው የሚጠቀሙበትን ባህር መንፈግ ከህግም ሆነ ከሞራል አንፃር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን እንዳለባት ገልጸው ይህንንም ማሳካት የትውልዱ አደራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መምህርት ፍረወይኒ ፍስሃ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የባህር በር ጥያቄው የታሪክ እውነታና የህግ ተቀባይነት ያለው፣ መልክዓ ምድርንና ፍትሃዊነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸው በሁሉም መመዘኛዎች የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት መብት ሊከበር ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም የትውልድ ጥያቄ የሆነው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ምላሽ ማግኘት ያለበት የህዝብ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።
በአክሱም ከተማ ነዋውና የህግ ባለሙያው አብራሃም አለማ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በህግም ይሁን በታሪክ ተቀባይነት ያለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ኢትዮጵያ በአቅራቢያዋ ባለው ቀይ ባህር የባህር በር ባለቤትነት መብቷ ሊከበር ግድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።