ቀጥታ፡

ምርታማነታቸው በምርምር የተረጋገጠ የቡና ዝርያዎች ለአልሚዎች ተላልፈዋል

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡- ሥነ-ምኅዳርን መሠረት በማድረግ ምርታማነታቸው በምርምር የተረጋገጠ ከ42 በላይ የቡና ዝርያዎች ለአልሚዎች መተላለፋቸውን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የቡናን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ከሚያስፈልጉ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ ምርጥ ዘርን መጠቀም መሆኑን ባለሥልጣኑ አስገንዝቧል።

በመረጣ እና በማዳቀል በጅማ ግብርና ምርምር ማዕከልና በሥሩ በሚገኙ ንዑስ የምርምር ማዕከላት አማካኝነት ሥነ-ምኅዳርን መሠረት ያደረጉ የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን በባለሥልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ደፈረስ ለኢዜአ ተናግረዋል።


 

በዚህም መሠረት ለደጋ አካባቢ ተስማሚ የሆኑ 14 የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን ጠቁመው፤ ምርታማነታቸውም በምርምር ማሳ ላይ በሔክታር ከ12 ነጥብ 2 እስከ 24 ነጥብ 41 ኩንታል መሆኑን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ለወይና ደጋ አካባቢ ተስማሚ የሆኑ 16 የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፤ የእነዚህ ቡና ዝርያዎች ምርታማነት ከ14 ነጥብ 8 እስከ 24 ኩንታል በሔክታር መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ለሞቃታማ (ዝቅተኛ) አካባቢ ተስማሚ የሆኑ 12 የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን ጠቅሰው፤ ከ13 ነጥብ 2 እስከ 25 ነጥብ 4 ኩንታል በሔክታር ምርት እንደሚያስገኙ አስታውቀዋል።


 

በሌላ በኩል አካባቢ በቀል የሆኑ ለወለጋ አካባቢዎች አራት፣ ለምዕራብ ሐረርጌ አራት፣ ለይርጋ ጨፌ ስድስት እና ለሊሙ አንድ የቡና ዝርያዎች መለቀቃቸውን ነው የተናገሩት።

የቡናን ምርታማነት በምርምር በማጎልበት ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም