የመንገድ መሠረተ ልማቱ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን ቀርፎልናል- የደጀን ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመንገድ መሠረተ ልማቱ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን ቀርፎልናል- የደጀን ወረዳ ነዋሪዎች
ደብረ ማርቆስ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡- የተገነባው የጠጠር መንገድ ትራንስፖርት ለማግኘትና ምርታቸውን በቀላሉ አጓጉዘው በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን በደጀን ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ተናገሩ።
የመንገድ ተደራሽነትን በማሳደግ የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን መንገድ መምሪያ ኃላፊ ማናየ አዳነ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ባለፉት አምስት ወራትም ከ780 ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር መንገድ አዲስ ግንባታና ጥገና በማካሄድ ለአገልግሎት መብቃቱን ጠቅሰው፤ ተንጠልጣይ ድልድይ መገንባቱንም አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት ቀበሌን ከቀበሌ፣ ወረዳን ከወረዳና ዞን ማዕከላት ጋር ማስተሳሰር ተችሏል ብለዋል።
በተሠራው ሥራ ትራንስፖርት በአቅራቢያቸው በማግኘታቸው ምርታቸውን በተሽከርካሪ አጓጉዘው በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን በደጀን ወረዳ የሽንቡሪ ቀበሌ ነዋሪ ምንዋጋው ያዜ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ትራንስፖርት ባለመኖሩ እናቶችና የጤና ችግር ያጋጠማቸውን ወደ ሕክምና ተቋም ለማድረስ እንቸገር ነበር፤ አሁን ግን መንገዱ በመገንባቱ የዘመናት ችግራችን ተቀርፏል ብለዋል።
የበረቅ ወርቅ አምባ ቀበሌ ነዋሪ ፈጠነ ይደግ በበኩላቸው፤ የተገነባው ተንጠልጣይ ድልድይ ለዘመናት በጎርፍ ምክንያት በሰውና እንስሳት ላይ ይደርስ የነበረውን ችግር ማስቀረቱን አንስተዋል።
የገጠር መንገድ ግንባታና ጥገናው የተከናወነው በመንግሥት፣ በሕብረተሰቡና ሌሎች አጋር አካላት ድጋፍ መሆኑንም ገልጸዋል።