ቀጥታ፡

ግብርናን ማዘመን እና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የመንግስት ቁልፍ አጀንዳ ነው- ሚኒስትር አዲሱ አረጋ 

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡- ግብርናን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የመንግስት ቁልፍ አጀንዳ ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ገለጹ። 

የግብርና ሜካናይዜሽንና የከተማ ግብርና ልማት ስትራቴጂዎች ላይ የባለድርሻ አካላት ምክክር እየተካሄደ ነው።


 

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።

መንግስት ዘርፉን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ብሎም በምግብ ራስን መቻልን ቁልፍ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።

የግብርና ሜካናይዜሽን ስትራቴጂ መዘጋጀቱ ግብርናው እንዲዘምንና የእሴት ሰንሰለቱን ከማሳጠር አኳያ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

መንግስት ግብርናውን ለማዘመን የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ማድረጉንና ትራክተሮችን ጨምሮ በርካታ ኮምባይነሮች ለአርሶ አደሩ ማድረሱን ተናግረዋል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት ስድስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በግብርና ሜካናይዜሽን ማልማት መቻሉን አመልክተዋል።

ከማሽነሪ ብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት የተለያዩ አማራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

የግብርና ሜካናይዜሽን ስትራቴጂ በአመለካከት ላይ ያለውን የተዛባ ግንዛቤ ለመፍታት እንዲሁም የማሽነሪ አጠቃቀም ላይ በቂ ስልጠና መስጠት ያስችላል ብለዋል።

የከተማ ግብርና የግብርና ልማት ስትራቴጂም የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ከምናሳካባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትሩ  ስትራቴጂው የከተማ መሬቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት አመታት በከተማ ግብርና በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው፣ ውጤቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ወጥነት ባለውና ተቋማዊ በሆነ መልኩ መደገፍ ይገባል ብለዋል።

በግብርና ትራንስፎርሜሽንና በከተማ ግብርና ልማት ስትራቴጂዎች ላይ ገለጻ እየተደረገ ሲሆን ባለድርሻ አካላት ግብዓት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በውይይት መድረኩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የፌዴራልና የክልል የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ አጋር አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም