ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለብሔራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ለስኬቱ የበኩላችንን እንወጣለን--የካፋ ሀገር ሽማግሌዎች

ቦንጋ፤ ታህሳስ 18/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለብሔራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ለስኬቱ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ የካፋ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

በሀገሪቱ ለግጭትና አለመግባባት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ለመፍትሄው እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

ኮሚሽኑ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አካታችና አሳታፊ የሆነ ምክክር ለማካሄድ የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በማከናወን ወደ መጨረሻው የውይይት ምዕራፍ ለመሸጋጋር ዝግጅት ላይ ነው። 

የምክክር ሂደቱን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የካፋ የሀገር ሽማግሌዎች በምክክር የሀገርን ችግር መፍታት ትልቅ እድል መሆኑን አንስተዋል።

የግጭት እንቅስቃሴ ከጉዳትና ውድመት በስተቀር ምንም ያመጣው ውጤት እንደሌለ ገልጸው የምክክር ሂደት ውጤቱ የሚያምርና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደረግ ነው ብለዋል።

የካፋ የሀገር ሽማግሌና ባህላዊ ንጉስ ኮላዎቾቺ ግርማ ኪዳኔ በምክክር አለመግባባ፣ ጠብና ቁርሾዎችን በእርቅ በመቋጨት ሰላምና አንድነትን ማጽናት እንደሚቻል ተናግረዋል።

በዚህ ደግሞ ማንም ቢሆን ተጠቃሚ እንጂ የሚጎዳ አለመኖሩን አንስተው በምክክር ለዘላቂ ሰላም እንዘጋጅ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለኮሚሽኑ ሥራ ውጤታማነት የሁሉም አበርክቶ ወሳኝ በመሆኑ በተለይ ወጣቱ የአባቶችን ምክር መስማት፣ መከባበር እና መደማመጥን ባህል ማድረግ አለበት ብለዋል።

ሌላኛው የካፋ የሀገር ሽማገሌ አድማሱ አቱሞ፤ ኢትዮጵያዊያን ችግሮችን በንግግርና በእርቅ የመፍታት የዳበረ ባህል ቢኖረንም እንደ ሀገር መክረን መፍትሄ በማምጣት ረገድ እስካሁን እድሉን አልተጠቀምንበትም ብለዋል።

በመሆኑም በሀገር ጉዳይ ከጫፍ ጫፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው የመምከር መልካም ዕድል በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የሀገር ሽማግሌ ጀማነህ ዘውዴ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ችግሮችን በንግግርና በውይይት መፍታት ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ጠንካራ ሀገር መገንባት በመሆኑ ለስኬቱ ሁላችንም የሚጠበቅብንን መወጣት አለብን ብለዋል።

ሀገራዊ አንድነትና ሰላምን የማጽናት ጉዳይ የጋራ ሃላፊነት በመሆኑ ሁሉም በቅንነትና ታማኝነት መሳተፍ እንዳለበት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 

የሀገር ሽማግሌዎቹ ለኮሚሽኑ ሥራ ውጤታማነት የሁሉም አስተዋፅኦ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፣ ምክክሩ ግቡን እስኪመታ ድረስ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም