በአፍሪካ ዋንጫ ናይጄሪያ ከቱኒዚያ ሴኔጋል ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዋንጫ ናይጄሪያ ከቱኒዚያ ሴኔጋል ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሰባተኛ ቀን ውሎ የምድብ ሶስት እና አራት ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።
በምድብ ሶስት ናይጄሪያ ከቱኒዚያ ምሽት አምስት ላይ በፌዝ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ናይጄሪያ ታንዛንያን 2 ለ 1 እና ቱኒዚያ ዩጋንዳን 3 ለ 1 አሸንፈዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።
የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ግንኙነታቸው ጋና እ.አ.አ በ1978 ባዘጋጀችው 11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበር። ቡድኖቹ በደረጃ ጨዋታ ተገናኝተው ናይጄሪያ በባባ ኦቱ መሐመድ ግቦች 2 ለ 0 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ሀገራቱ በአህጉራዊው መድረክ ለመጨረሻ ጊዜ እርስ በእርሳቸው የተጫወቱት ካሜሮን እ.አ.አ በ2022 ባዘጋጀችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው። በጥሎ ማለፍ ላይ ተገናኝተው ቱኒዚያ በዩሱፍ ምሳክኒ ጎል 1 ለ 0 በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አልፋለች።
ናይጄሪያ እና ቱኒዚያ በአፍሪካ ዋንጫው ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ናይጄሪያ አራት ጊዜ ስታሸንፍ ቱኒዚያ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቶታል።
የሚያሸንፈው ቡድን ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱን ያረጋግጣል። ናይጄሪያ የአፍሪካ ዋንጫን ሶስት ጊዜ፣ ቱኒዚያ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።
በምድብ አንድ ሌላኛው መርሃ ግብር ዩጋንዳ ከታንዛንያ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ በአል መዲና ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ብሄራዊ ቡድኖቹ በመጀመሪያ ጨዋታ ካስተናገዱት ሸንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
በተያያዘም የምድብ አራት ጨዋታዎችም ዛሬ ይደረጋሉ።
ሴኔጋል ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በታንጀር ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
በምድቡ የመጀመሪያ መርሃ ግብር ሴኔጋል ቦትስዋናን 3 ለ 0፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ቤኒን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
ሀገራቱ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ጨዋታዎችን እርስ በእርስ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1968 ባዘጋጀችው ስድስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ተገናኝተው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ማሊ እ.አ.አ በ2002 ባዘጋጀችው 23ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው ተገናኝተው ሴኔጋል 2 ለ 0 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች። አሸናፊው ቡድን ጥሎ ማለፉን ይቀላቀላል።
ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫን አንድ ጊዜ ያነሳች ሲሆን ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።
በዚሁ ምድብ ቤኒን ከቦትስዋና ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሁለቱ ሀገራት የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት ይፋለማሉ።