በሴቶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና ዛሬ ይጫወታሉ።
ጨዋታው በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች በዘጠኙ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ 29 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሶስት ጎሎችን አስተናግዷል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ29 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በሊጉ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ በአምስቱ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።
በ12ቱ ጨዋታዎች ላይ 14 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ሲዳማ ቡና በ18 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዛሬውን ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ ያደርጋል።
በአንጻሩ ሲዳማ ቡና ድል ከቀናው ደረጃውን ከሰባተኛ ወደ ስድስተኛ ከፍ ያደርጋል።
የቡድኖቹ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በነበረው ተሳትፎ ምክንያት የተራዘመ ነው።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በያዝነው ሳምንት የመጀመሪያ ተስተካካይ ጨዋታውን ከሸገር ከተማ አድርጎ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።