የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋቾች - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋቾች
ከኢትዮጵያዊው ኮከብ መንግስቱ ወርቁ እስከ ናይጄሪያዊው ዊሊያም ትሮስት-ኤኮንግ፤ የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋቾች
እ.አ.አ በ1957 የተጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ የአህጉሪቷ ቁንጮ የእግር ኳስ መድረክ ሆኖ ለሰባት አስርት ዓመታት ጸንቶ ቆይቷል። ውድድሩ በአፍሪካ እግር ኳስ ያሉ ምርጥ ብሄራዊ ቡድኖች እና እምቅ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች የሚታይዩበት ነው። አፍሪካ ዋንጫ ለሀገራት ዋንጫ ብቻ የሚሸልም መድረክ አይደለም በውድድሩ ድንቅ የግል ብቃታቸውን ላሳዩ ተጫዋቾች እውቅና እና ሽልማት ያበረክታል።
ከሽልማቱ አንዱ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሽልማት ነው። በ68 ዓመታት የውድድሩ ታሪክ የዘንድሮውን ሳይጨምር 34 ተጫዋቾች ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጠዋል።
የኮከብ ተጫዋች ሽልማት በውድድሩ ላይ ትልቅ ተጽእኖ የፈጠሩ እና ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩ ተጫዋቾች እውቅና የሚያገኙበት ነው። ከግብጻዊው መሐመድ ዲያብ አልታር (በቅጽል ስሙ አድ-ዲባ) አንስቶ እስከ ናይጄሪያዊው ዊሊያም ትሮስት-ኤኮንግ የግል ክብሩን ወስደዋል።
ሱዳን እ.አ.አ በ1957 ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ነበረች። በውድድሩ ሱዳንን ጨምሮ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ተሳትፈዋል። በውድድሩ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ግብጽ ኢትዮጵያን 4 ለ 0 አሸንፋለች። በፍጻሜው መሐመድ ዲያብ አልታር አራት ግቦችን አስቆጥሯል። በውድድሩ ታሪክ የመጀመሪያውን ሀትሪክ የሰራ እና ከአራት ግቦችን ያስቆጠረ ተጫዋች ሆኗል።
አልታር በውድድሩ አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ከመሆኑ በተጨማሪ የውድድሩ የመጀመሪያው ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።
ግብጽ እ.አ.አ በ1959 ራሷ አዘጋጅታ ራሷ ባነሳቸው ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሀገሩ ዜጋ የሆነው መሐሙድ ኤል-ጎሃሪ ባሳየው ብቃት ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1962 ባዘጋጀችው ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ አጥቂው መንግስቱ ወርቁ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። ይህም መንግስቱ ወርቁ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ኮከብ ተጫዋች የሆነ የተመረጠ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል። ታዋቂው አጥቂ ኢትዮጵያ በፍጻሜው ጨዋታ ግብጽን 4 ለ 2 ያሸነፈችበትን ጨዋታ ላይ ያስቆጠራትን ጎል ጨምሮ በውድድሩ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። መንግስቱ ወርቁ ኢትዮጵያ ታሪካዊውን ዋንጫ እንድታነሳ ትልቁን ሚና ተጫውቷል።
መንግስቱ ወርቁ በስድስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ 17 ጨዋታዎችን አድርጎ 10 ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ከምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች መካከል ይጠቀሳል።
ካሜሮናዊው ሮጀር ሚላ እና ግብጻዊ አህመድ ሀሰን በአፍሪካ ዋንጫ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ኮከብ ተጫዋች ሆነው ተመርጠዋል።
ሮጀር ሚላ ግብጽ እ.አአ በ1986 ባዘጋጀችው 15ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያውን የኮከብ ተጫዋች ሽልማት አገኝቷል። ሀገሩ ካሜሮን በፍጻሜው በግብጽ ብትሸንፍም ሚላ ለካሜሮን ያበረከተው አስተዋጽኦ ወሳኝ የሚባል ነበር። አራት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆንም ችሏል።
ካሜሮናዊው አጥቂ እ.አ.አ በ1988 በሞሮኮ በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሀገሩ ዋንጫ እንድታነሳ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ካሜሮን በፍጻሜው ናይጄሪያን በጄሮም ኩንቴ ግብ 1 ለ 0 ስታሸንፍ ተላፊ ነበር። በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ከኮትዲቯሩ አብዱላዬ ትራኦሬ፣ ከአልጄሪያው ላክዳር ቤልሆሚ እና ከግብጹ ገማል አብደልሃሚድ ጋር በጋራ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አስቆጥሯል።
ሌላኛው ሁለት ጊዜ የኮከብ ተጫዋችነት ሽልማት ያገኘው ተጫዋች ግብጻዊው አህመድ ሀሰን ነው።
ግብጽ እ.አ.አ በ2006 ባዘጋጀችው 25ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኮትዲቯርን በመለያ ምት በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች። በወቅቱ አራት ግቦችን ያስቆጠረው የፈርኦኖቹ አጥቂ አህመድ ሀሰን በውድድሩ ላይ ባሳየው ድንቅ ብቃት ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጧል።
እ.አ.አ በ2010 በአንጎላ አስተናጋጅነት በተካሄደው 27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ግብጽ ጋናን በማሸነፍ ዋንጫውን ለሰባተኛ ጊዜ አንስታለች። አጥቂው አህመድ ሀሰን አሁንም የውድድሩ ኮብ ተጫዋች ሆኗል። በውድድሩ ላይ ሶስት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ወሳኝ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ከ34ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የኮከብ ተጫዋቾች ሽልማት ውስጥ ግብጽ እና ካሜሮን በተመሳሳይ ሰባቱን በመውሰድ ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል።
መሐመድ ዲያብ አልታር (በቅጽል ስሙ አድ-ዲባ) ፣ አህመድ ሀሰን፣ ሀሰን ኤል-ሻዝሊ፣ መሐሙድ ኤል-ጎሃሪ እና ሆስኒ አብድ ራቦ ሽልማቱን ያገኙ የግብጽ ተጫዋቾች ናቸው።
ሮጀር ሚላ፣ ሪጎበርት ሶንግ፣ ጂን-ፒየር ቶኮቶ፣ ቲኦፓል አቤጋ፣ ላውረን እና ክርስቲያን ባሶንግ የግል ክብሩን ማሸነፍ ችለዋል።
የምዕራብ አፍሪካውያኑ ጋና እና ናይጄሪያ በተመሳሳይ አራት ተጨዋቾች የኮከብ ተጫዋችነት ሽልማቱን አግኝተዋል።
አቢዲ ፔሌ፣ ኦሲ ኮፊ፣ ካሪም አብዱል ራዛቅ እና ክርስቲያን አትሱ ሽልማቱን የወሰዱ የጋና ተጫዋቾች ናቸው።
ጄይ ጄይ ኢኮቻ፣ ራሺድ ያኪኒ፣ ክርስቲያን ቹኩ እና ዊሊያም ትሮስት-ኤኮንግ ከናይጄሪያ ሽልማቱን ወስደዋል።
ከዛምቢያ ካሉሻ ቡዋሊያ እና ክሪስቶፈር ካቶንጎ፣ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ካዛዲ ምዋምባ እና ንዳዬ ሙላምባ እንዲሁም ራህባ ማጄር እና ኢስማኤል ቤናሰር ከአልጄሪያ ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጠዋል።
መንግስቱ ወርቁ (ኢትዮጵያ)፣ ቤኒ ማካርቲ (ደቡብ አፍሪካ)፣ ሳዲዮ ማኔ (ሴኔጋል)፣ ላውረን ፖኩ (ኮትዲቯር)፣ ፋውዚ አል-ኢሳዊ (ሊቢያ) እና ጆናታን ፒትሮፓ (ቡርኪናፋሶ) በተመሳሳይ አንድ አንድ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆነው መመረጥ ችለዋል።
35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል። የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ማን ይሆናል? የሚለው ጉዳይ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል።