የድሬዳዋ አሥተዳደር ያደረገልን አቀባበል አብሮነትን ያጎለብታል - የዓመታዊ የቁልቢ ገብርኤል ንግሥ በዓል ተጓዦች - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ አሥተዳደር ያደረገልን አቀባበል አብሮነትን ያጎለብታል - የዓመታዊ የቁልቢ ገብርኤል ንግሥ በዓል ተጓዦች
ድሬዳዋ፤ ታኅሣስ 17/2018 (ኢዜአ)፡- የድሬዳዋ አሥተዳደር ያደረገልን አቀባበል አብሮነትን ያጎለብታል ሲሉ ዓመታዊውን የቁልቢ ገብርኤል የንግሥ በዓል ለማክበር ወደ ሥፍራው ያቀኑ ተጓዦች ተናገሩ።
ከነገ በስቲያ ለሚከበረው ዓመታዊ የቁልቢ ገብርኤል የንግሥ በዓል ወደ ሥፍራው እያቀኑ ላሉ እንግዶች የድሬዳዋ አሥተዳደር አቀባበል አድርጓል።
በዚሁ ወቅት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ እንግዶች፤ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና መስተንግዶ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም አብሮነትን የሚገነባ በጎ ተግባር መሆኑን ነው ያስረዱት።
በአሥተዳደሩ አመራሮችና ነዋሪዎች ለተደረገላቸው አቀባበል ምሥጋናቸውን አቅርበው ሁነቱን ሁልጊዜም እንደሚያስታውሱት ጠቅሰዋል።
ዘመንን የተሻገረው የአንድነትና የአብሮነት ትስስር በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አሥተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።
ድሬዳዋ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት መገለጫ ናት ያሉት ከንቲባው፤ ይህም በዓሉን ለማክበር እየመጡ የሚገኙ እንግዶችን በመቀበል መንፀባረቁን አስገንዝበዋል።
በዓመት ሁለት ጊዜ በሚከበረው በዓል ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትንና ትስስርን በማጠናከር የወል ትርክትን ለማነፅ ወሳኝ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
የአሥተዳደሩ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ በበኩላቸው፤ በዓሉን በድምቀት ለማክበርም ፖሊስና የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል።