ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞችን የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ቅንጅታዊ ሥራ ይጠናከራል

ጅማ ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦የአካል ጉዳተኞችን የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ በቅንጅት የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስአቢሊቲስ ኤንድ ዴቫሎፕመንት ድርጅት ጋር በትብብር ያዘጋጀውና የአካል ጉዳተኞችን የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ የምክክር መድረክ ዛሬ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የአካል ጉዳተኞችን የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ለግብአት አቅርቦትና ለመሰረተ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ትምህርት ስርአት እንዲኖራቸው ከማድረግ ጀምሮ ቴክኖሎጂን የማሟላት ሥራው ትኩረት ተሰጥቶት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል ዲን ደሳለኝ በየነ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኞችን  የትምህርት አቀባበል ለማሳደግ ለግብአት አቅርቦትና ለመሰረተ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።


 

አካታችና ሁሉን አቀፍ የትምህርት አሰጣጥ ለመተግበርም በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ሥርአት መዘርጋቱን ነው የገለጹት።

አካል ጉዳተኞችን ያማከለ የትምህርት የመሰረተ ልማትና የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስአቢሊቲስ ኤንድ ዴቫሎፕመንት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ስምኦን (ዶ/ር) ናቸው።


 

ለተግባራዊነቱም ተቋሙ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና ግብአትን በማሟላት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የመማር ማስተማር ምህዳር እንዲፈጠር ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

አካታች የትምህርት ስርአትን በማጠናከር አካል ጉዳተኞች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ አካል ጉዳተኞች በበኩላቸው፤ የአካል ጉዳት ያለባቸው ተማሪዎችን የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ዘለቀ ሽፈራው፣ ዩኒቨርሲቲው አካል ጉዳተኞች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የዘረጋው ቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት የሚበረታታ መሆኑን ተናግሯል።

የአካል ጉዳተኞችን ውጤታማነት ለማሳደግ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ በታችኛው የትምህርት እርከንም ጠንካራ ሥራ መስራት ይገባል ብሏል።

አካል ጉዳተኞችን በማብቃቱ ሥራ ወላጆችና ማህበረሰቡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግሯል።

በመድረኩ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ እንግዶች፣ አካል ጉዳተኞችና የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም