ቀጥታ፡

በማዕድን ልማት የተፈጠረው ምቹ የአሰራር ምኅዳር የዘርፉን ምርታማነት እያሳደገ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ በማዕድን ልማት የተፈጠረው ምቹ የአሰራር ምኅዳር የዘርፉን ምርታማነት እያሳደገ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

በተያዘው የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ባለፉት ወራትም 30 ኩንታል የወርቅ ምርት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንደቻለም ቢሮው አስታውቋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ናስር መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንግስት ለብዝኅ ኢኮኖሚ የሰጠው ትኩረት የክልሉን የማዕድን ጸጋ ለማልማት ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

በክልሉ የማዕድን ሃብት ምርታማነት ላይ የተፈጠረው ማንሰራራትም ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና እንዲወጣ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የማዕድን ሃብት ልማትን ለማሻሻል የተዘረጋው ምቹ የአሰራር ሥርዓት ምኅዳርም የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ የኢኮኖሚ አቅም እንዲሆን አስችሏል ነው ያሉት።

ለአብነትም የማዕድን ሃብት ምርታማነትን ለማሻሻል ተግባራዊ የተደረገው ፖሊሲና ስትራቴጂ የዘርፉን ኢንቨስትመንት በሕጋዊ ማዕቀፍ በመምራት እመርታዊ ለውጥ እንዲመዘገቡ ማድረጉን አስረድተዋል።

የመደመር መንግሥት የብዝሃ ዘርፎች ዕይታም በክልሉ በጥናት ላይ የተመሰረተ የማዕድን ሀብት ልማት በማከናወን ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል።

ይህም ክልሉ ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክትበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከለውጡ ወዲህ የማዕድን ልማትን የሚያስተባብሩ ተቋማትን እስከ ወረዳ ድረስ በማደራጀት ከፍተኛ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

በዚህም የማዕድን ልማቱ ከፍተኛ መነቃቃት ማሳየቱን ጠቅሰው፥ ለአብነትም በተያዘው 2018 በጀት ዓመት ባለፉት ወራት ብቻ 30 ኩንታል ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም