ቀጥታ፡

የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፖሊሲ ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር ተጣጣሚ በሆነ መልኩ የተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፖሊሲ ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር ተጣጣሚ በሆነ መልኩ መዘጋጀቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፥ የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲን አስመልክቶ ከዲጂታል ካውንስል አባላት ጋር በበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በሁሉም መስክ የሥራ ፈጠራ ባህልን በማስረጽ ቀጣይነት ያለው እና ፈጣን ዕድገትን ዕውን ለማድረግ ኢንተርፕረነርሽፕ ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለዋል።

ፖሊሲው በዋናነት ሁሉን አቀፍ እና አካታች ሀገራዊ የኢንተርፕረነርሽፕ ንቅናቄን በማቀጣጠል በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር ተጣጣሚ በሆነ መልኩ የዲጂታል ሥራ ፈጠራንና ተወዳዳሪነትን የሚያበረታታና የሚደግፍ መሆኑን አመልክተዋል።

የፖሊሲ ማዕቀፉ ችግር ፈች ማህበረሰብን ለመገንባት፣ የፈጠራ ባህልን ለማጎልበት፣ እሴትን ለመጨመር እንዲሁም ምቹ ስነምህዳርን ለመገንባት የሚያስችል የኢኮኖሚ ዕድገት ማዕቀፍ እንደሆነም ተናግረዋል።


 

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያን የኢንተርፕረነርሽፕ ስነ-ምህዳርና የስራ ፈጠራ ውጥኖችን አቅጣጫ በመስጠት የመምራት ቁልፍ ሚና አለው ነው ያሉት።

በተለይ የኢንተርፕረነርሽፕ ስነ-ምህዳሩን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የጋራ አመለካከቶችን፣ እምነቶችንንና ባህሪያትን ለማጎልበት በእጅጉ እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

በውይይቱ የልማት ፖሊሲው የታለመለትን ውጤት ማምጣት እንዲችል በፖሊሲው ትግበራ ወቅት የሚታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን በመለየት በየደረጃው ወጥና ጠንካራ የክትትል ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ከዲጂታል ካውንስሉ ጋር መግባባት መፈጠሩን ገልጸዋል።

በኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ እና ግብዓቶችን በመጨመር የልማት ፖሊሲ ሰነዱ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኮ እንዲፀድቅ መወሰኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም