መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ትርክትን ለመገንባት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ትርክትን ለመገንባት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙሃን የሀገር ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና የብሔራዊነት ትርክትን ለመገንባት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ገለጹ።
48ኛው የ"ጉሚ በለል" የውይይት መድረክ "ብሔራዊ ጥቅም እና መገናኛ ብዙሃን" በሚል መሪ ሐሳብ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ተካሂዷል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በዚሁ ወቅት፤ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም በትውልድ የማይገደብ መሆኑን ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ገልጸው፤ የሕዝብ አንድነትን ለማጠናከር እንዲሁም የኢትዮጵያን ተደማጭነት ለማሳደግ ግንባር ቀደም ሚናቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
ለብሔራዊ ትርክት ግንባታ እና ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል በትኩረት መሥራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮችም ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ የማይተካ ሚና አላቸው።
ስለሆነም መገናኛ ብዙሃን ለሀገር እና ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ነው ያመለከቱት።
መገናኛ ብዙሃን ለገጽታ ግንባታ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኃይሉ፤ በጎ ገጽታን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ለዚህ ስኬት ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መታጠቅ እንዲሁም የሰለጠነ የሰው ሃይል ማሟላት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም መገናኛ ብዙሃን ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበርና ሉዓላዊነት መጠበቅ ሚናችንን እናጠናከራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የመገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ ተግባር መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም አኳያ ኢዜአ የሀገርን ገጽታ የሚገነቡ፣ ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎችን በግንባር ቀደምትነት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቢንያም ኤሮ፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ከምንም በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ተቋማቸው ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ የይዘት ስራዎችን በመሥራት የብሔራዊ ትርክትን ለመገንባት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው፤ መገናኛ ብዙሃን በተደመረ አቅም ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር በጋራ መትጋት አለባቸው ብለዋል፡፡
የኤን ቢሲ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ከበደ በበኩላቸው፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከሀገር ብሔራዊ ጥቅም አኳያ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስልጠና እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የኦቢኤን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ በላይነህ ፤ መገናኛ ብዙሃን ማስገንዘብ፣ የማጋለጥ እና የመከላከል ሚናውን ማጠናከር አለበት ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት እና በኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ትብብር የሚዘጋጀው የ"ጉሚ በለል" መድረክ በተለያዩ ወቅታዊና ስትራቴጂካዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ምሁራንና የሥራ ኃላፊዎች የሚወያዩበት መድረክ ነው።